Wednesday, October 23, 2013

ብረታ ብረት ኮርፖሬሽንና ሚድሮክን ጨምሮ 20 ድርጅቶች እንዳይፈተሹ ያደረጉ ከፍተኛ የሙስና ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ



ብረታ ብረት ኮርፖሬሽንና ሚድሮክን ጨምሮ 20 ድርጅቶች እንዳይፈተሹ ያደረጉ ከፍተኛ የሙስና ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

አቶ መላኩ ፈንታ የሦስት ልጆች እናትን አፋተው አግብተዋል ተባለ 
-አቶ ጌቱ ገለቴን ጨምሮ 12 ተከሳሾች በሌሉበት ክሳቸው ተሰማ
በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ከግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. መጀመሪያ ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ክስ ተመሥርቶባቸዋል የተባሉት
ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች፣ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ሚድሮክን ጨምሮ 20 ድርጅቶች ከውጭ ዕቃ ሲያስመጡ እንዳይፈተሹ አድርገዋል በሚልና በተለያዩ የሙስና ድርጊቶች የተካተቱበት የክስ ቻርጅ፣ ጥቅምት 11 እና 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ከአንድ ወር ከ15 ቀናት ቆይታ በኋላ ተነበበላቸው፡፡ 
ክሱን የመሠረተው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ በተለያዩ ሦስት የክስ መዝገቦች በድምሩ በ55 ተጠርጣሪዎችና በአምስት ድርጅቶች ላይ ያዘጋጀውን የክስ ቻርጅ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት አቅርቦ አሰምቷል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደዘረዘረው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ፣ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የአዳማ ቅርንጫፍ የሕግ ማስከበር ኃላፊ አቶ ተመስገን ሥዩም፣ የአቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ የሕግ ማስከበር ኃላፊና በሚሌና አካባቢው ያሉ ፍተሻ ጣቢያዎች ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ግረፍና የአዳማ ቅርንጫፍ የፍተሻ ክፍል ኃላፊና አጠቃላይ የቅሬታ ቡድን አስተባባሪ አቶ ያለው ቡላ በዋና ወንጀል አድራጊነትና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ገለጻ፣ ባለሥልጣናቱና ኃላፊዎቹ በመንግሥትና በሕዝብ በተጣለባቸው ከፍተኛ ኃላፊነት የመንግሥት ግብር እንዲሰበሰብ ማድረግ ሲገባቸው፣ በተቃራኒው በመሥራት የመንግሥት ቀረጥና ታክስ እንዳይከፈል አድርገዋል፡፡ የተከለከሉ ዕቃዎች እንዳይገቡ በፍተሻ የሚለይበት ሥርዓት እንዳይፈጠር አድርገዋል፡፡ ሕገወጥ አስመጭዎች እንዳይጠየቁ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እንዲመቻች በማድረግ ድርጅቶች (አስመጪዎች) ተመርጠው ሳይፈተሹ እንዲያልፉ አድርገዋል፡፡ የተለያዩ አስመጭዎችና ትራንዚተሮች ሕገወጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጉቦና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም የመቀበል፣ የመስጠትና የማቀባበል ወንጀል እንዲፈጽም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠራቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 
ከአቶ መላኩና ከአቶ ገብረዋህድ፣ ለባለሥልጣኑ የሚሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅና በሚሌ ቅርንጫፍ ሥር የሚገኙትን የጋላፊ መቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ የሰመራ ደረቅ ወደብ ጣቢያ፣ የሚሌ የዘመናዊ ማሽን መፈተሻ ጣቢያና የአዋሽ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ እሸቱ ግረፍ ትዕዛዝ ይተላለፍላቸው እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ 
በትዕዛዙ መሠረት ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ የትራንዚት ፈቃድ ተሰጥቷቸው በጂቡቲ ወደብ በኩል ከውጭ አገር የሚገቡ ዕቃዎች ሚሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሲደርሱ በአቶ እሸቱ ግረፍ አማካይነት ተመርጠው ሳይፈተሹ ‹‹ተፈትሸዋል›› የሚል ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ 
ሳይፈተሹ ‹‹ተፈትሸዋል›› የሚል ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ የተለያዩ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ያስገቡት ድርጅቶች ኒያላ ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያና መለዋወጫ ዕቃ አስመጪ፣ ፔትራም፣ ሞኤንኮ፣ ጌታስ ትሬዲንግ፣ አልሳም፣ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ አይካ አዲስ (የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ)፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ፣ ሆላንድ ካርስ (ከስሮ ተዘግቷል)፣ ቶታል ኢትዮጵያ፣ ሚድሮክ፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ ድሬ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ፣ ኢትዮ ሌዘር፣ ኢትዮ ቆዳ ፋብሪካ፣ ባሰፋ ትሬዲንግ፣ ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ጌታስ ኢንተርናሽናልና ኮሜት ትሬዲንግ መሆናቸው በክሱ ተዘርዝረዋል፡፡ 
አቶ ጌቱ ገለቴ የጌታስ ትሬዲንግና ጌታስ ኢንተርናሽናል ባለቤት (በሌሉበት)፣ አቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ (የኮሜት ትሬዲንግ ሀውስ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ) አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር (የባስፋና ነፃ ትሬዲንግ ባለቤት)፣ አቶ ከተማ ከበደ (የኬኬ ድርጅት ባለቤት) ከነድርጅቶቻቸው በክሱ ውስጥ የተካተቱ ሲሆኑ፣ ከላይ የተዘረዘሩት ድርጅቶችም ሆኑ ባለቤቶቻቸው በክሱ አልተካተቱም፡፡ አቶ ጌቱ ገለቴ ከአቶ መላኩና ከአቶ ገብረዋህድ ጋር ባላቸው ግንኙነት ወደ አገር ውስጥ የተለያዩ ዕቃዎችን ሲያስገቡ በሕግ አግባብ መሠረት ተፈትሸው ተገቢውን ታክስና ቀረጥ መክፈል ሲገባቸው፣ በሕገወጥ ትዕዛዝ አማካይነት ዕቃዎቻቸው ሳይፈተሹ ‹‹ተፈትሸዋል›› የሚል የማረጋገጫ ኢንቮይስ ተስተናግደው ሕገወጥ ጥቅም ማግኘታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 
ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በተነበበው ክስ ውስጥ 31 ተጠርጣሪዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ባጠቃላይ 28 ክሶች ቀርበዋል፡፡ በክሶቹ ውስጥ በዝርዝር በተገለጹት በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎችና ከ20 በላይ የሚሆኑ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና ዋና መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎችና ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር በተለያዩ ቦታዎች ጉቦ የተቀበሉ መሆኑን፣ በፍተሻ ወቅት እንደተፈተሸ አድርጎ በማሳለፍና የተሳሳተ ሰነድ በመጠቀም በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች መልኩ በመምራትና በዋና ወንጀል አድራጊነትና የሙስና ወንጀል በመፈጸም ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ 
በሦስቱም የክስ መዝገቦች ላይ ተጠርጥረው ስማቸው የተጠቀሰው አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. በተነበቡ ሁለት የክስ መዝገቦች ላይም የመጀመሪያው ተጠሪ ሆነው ተከሰዋል፡፡ 18 ሰዎች የተካተቱበት የክስ መዝገብ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ሹማምንትና ኃላፊዎች የተካተቱበት ሲሆን አቶ አመሐ ዓባይ፣ አቶ ነብዩ ሳሙኤል፣ አቶ አስፋው ወሰን አለነ፣ አቶ ተስፋዬ መርጊያ፣ አቶ አማረ ገብረወልድ፣ አቶ መስፍን አህመድ፣ አቶ ደሜ አበራ፣ አቶ ተስፋዬ ቤተና ወ/ሮ ሃይማኖት ዓለሙ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በክሱ የተካተቱ ቢሆንም ክሱ የተሰማው በሌሉበት ነው፡፡ 
አቶ መላኩ፣ አቶ ገብረዋህድ፣ የባለሥልጣኑ የኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላቸው በየነና በሌሉበት የተከሰሱት የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀል የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው፣ ከታክስ ገቢ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ማስተናገድ የሚያስችሉ አዋጆችና አጣሪ ኮሚቴ ቢኖርም፣ አቶ መላኩ በአዋጁ መሠረት የቀረቡ አቤቱታዎችን እንደገና መከለስ የሚያስችል ሕገወጥ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ ሕገወጥ ድርጊቱን መፈጸም የሚያስችል መመርያም አውጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሀዋስ አግሮ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ድርጅት በሕገወጡ መመርያ መሠረት አቤቱታ እንዲያቀርብ በማድረግና ሕገወጡ ኮሚቴ እንዲያየው በማድረግ ከ22.3 ሚሊዮን ብር በላይ መንግሥት እንዲያጣ ማድረጋቸውን ክሱ ይተነትናል፡፡ አቶ ገብረዋህድም ለዚሁ ድርጅት በሕገወጥ መንገድ ድጋፍ በማድረግና ካልተያዙት ተጠርጣሪዎች (የሕገወጥ ኮሚቴ አባላት ናቸው) ጋር በመተባበር የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ሼባ ስቲል ሚልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የንግድ ትርፍ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስና  ከተከፋዩ ሒሳብ የሚቀነስ ግብር ኦዲት ተደርጎ 101.4 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ከተወሰነበት በኋላ፣ ለሕገወጡ ኮሚቴ አቤቱታ እንዲያቀርብ በማድረግ፣ አቶ ገብረዋህድ እንዳይከፍል ማድረጋቸውን ክሱ ይጠቅሳል፡፡ ለሌሎችም በርካታ ድርጅቶች ላይ ግብር እንዳይሰበሰብ ማድረጋቸውን ክሱ በዝርዝር ያብራራል፡፡ 
17 ክሶችን በያዘው መዝገብ ውስጥ አቶ መላኩ ፈንታ የሦስት ሕፃናት እናትን ከትዳራቸው በማፋታት እንዳገቧት የሚገልጽ ክስም ተካቷል፡፡ የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያብራራው፣ አቶ ደምሴ ዓለማየሁና ወ/ሮ መቅደስ ለማ ከኅዳር 8 ቀን 1993 ዓ.ም. ጀምሮ ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ ሦስት የዘጠኝ፣ የአምስትና የሁለት ዓመት ሕፃናትንም አፍርተዋል፡፡ ወ/ሮ መቅስና አቶ ደምሴ ሳንክቹሪ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ድርጅት አቋቁመው እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. አቶ ደምሴ ግብር ለመክፈል ሲሄዱ 144,000 ብር እንዲከፍሉ ይነገራቸዋል፡፡ ግብሩ የበዛባቸው አቶ ደምሴ ቅድሚያ ይከፍሉና ለምሥራቅ አዲስ አበባ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ጉዳዩ መፍትሔ ሳያገኝ ከአንድ ዓመት በላይ በመፍጀቱ ባለቤታቸው ወ/ሮ መቅደስ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ያቀረቡትን አቤቱታ ለአቶ መላኩ በግልባጭ ሊሰጡ ወደ ቢሮአቸው ያመራሉ፡፡ አቶ መላኩ በወቅቱ የነበራቸውን ሥልጣን መከታ በማድረግ በሚያዝያ ወር 2002 ዓ.ም. አካባቢ ከተገመተባቸው ግብር ላይ 100 ሺሕ ብር እንዲቀነስ ማድረጋቸውንና ወ/ሮ መቅደስን ማማገጥ መጀመራቸውን፣ በተለያዩ ጊዜያት በሾፌራቸው አማካይነት ወደ ባህር ዳር በመውሰድ ሰመርላንድ ሆቴል ለሦስትና ለሰባት ቀናት መቆየታቸውን፣ እንዲሁም በመንግሥት ተሽከርካሪና ነዳጅ በመጠቀም ሴትየዋን ሲያዝናኑ መክረማቸውን ክሱ ዘርዝሯል፡፡ በመጨረሻም ወ/ሮ መቅደስን ከትዳራቸው በማፋታትና ልጆቻቸውን ያለአሳዳጊ በመበተን አግብተዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በፈጸሙት የማፋታት፣ ልጆችን ያለ አሳዳጊ እንዲቀሩ የማድረግና በፈጸሙት የሥልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
በአጠቃላይ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሹማመንትና ኃላፊዎች ግብር እንዳይሰበስብ በማድረግ፣ በመቀነስ፣ ፍተሻ እንዳይኖር በማድረግ፣ በተለያየ ቦታ መጠኑ የተለያየ ጉቦ በመቀበልና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ ያነበበውና 93 ክሶችን ያካተተው የክስ መዝገብም ከአቶ መላኩ፣ ከአቶ ገብረዋህድና ባለቤታቸው ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ በተጨማሪ፣ ምክትል ዋና ዓቃቤ ሕግ የነበሩትን አቶ መርክነህ ዓለማየሁ፣ አቶ አስመላሽ ወልደማርያም፣ አቶ ስማቸው ከበደ (የኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ባለቤት)፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአገር ውስጥ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤልን ጨምሮ በድምሩ 24 ተከሳሾችን በክሱ አካቷል፡፡
አቶ መላኩና አቶ ገብረዋህድ በአቶ ከተማ ከበደ ላይ ቀርቦ የነበረን የአራጣ ማበደር ወንጀል ክስ በማቋረጥ፣ አቶ በላቸው ደግሞ አቶ ስማቸው ከበደ ለኢንተርኮንቴንታል ሆቴል ከቀረጥ ነፃ የ9.9 ሚሊዮን ብር ዕቃዎች ከውጭ አስገብተው ለተፈለገው ዓላማ አለማዋላቸው እየታወቀ በድጋሚ እንዲቆጠር፣ ድርጅቱ በምርመራ እንዳይጣራና በወንጀል እንዳይከሰስ ሁኔታዎችን በማመቻቸታቸው፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች ሁኔታ በመሥራት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ይተነትናል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም ከአቶ መላኩና ከአቶ ገብረዋህድ ጋር በመመሳጠር ተከሰው ተመሥርቶባቸው የነበረውን ክስ እንዲቋረጥላቸው ማድረጋቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡ 
አቶ ገብረዋህድ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ሃይማኖት ጋር በጋራ በቀረበባቸው ክስ፣ አቶ ገብረዋህድ ከ1978 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በመንግሥት ሠራተኝነታቸው ከ247 ብር እስከ 5,700 ብር ይከፈላቸው ነበር፡፡ ኮሎኔል ሃይማኖት ደግሞ ከ1989 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ በመከላከያ ተቀጥረው ሲሠሩ ከ790 ብር እስከ 2,145 ብር ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በተደረገ ብርበራ በተለያዩ ባንኮች የተቀመጠ ከፍተኛ ገንዘብ፣ ተሽከርካሪዎች፣ መቀሌና አዲስ አበባ ውስጥ ቤቶች፣ የተለያዩ አገሮች ገንዘቦች፣ ሰባት ሽጉጥና ሁለት ታጣፊ ክላሽ መገኘቱን ክሱ ይዘረዝራል፡፡ አቶ መርክነህ ዓለማየሁም ምርመራ እንዲቋረጥ፣ ከአቶ ባህሩ አብርሃ (ብስራት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) 100 ሺሕ ብር ጉቦ መቀበልና ከተከሰሱበት ክስ በነፃ በማሰናበት፣ ከ1987 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ከ2,535 ብር እስከ 10,234 ብር ያገኙ የነበረ ቢሆንም፣ ከደመወዛቸው ጋር የማይመጣጠን ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አካብተው በመገኘታቸውና ሌሎችም ክሶች ተመሥርተውባቸዋል፡፡
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ ከ1,600 እስከ 6,000 ብር ደርሶ እንደነበር ክሱ ጠቅሶ፣ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን በ175 ካሬ ሜትር ላይ ባለሦስት ፎቅ ቤት ገንብተው በ50 ሺሕ ብር ማከራየታቸውን፣ የመንግሥት ይዞታ የነበረና የሊዝ ግምቱ 2.9 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 375 ካሬ ሜትር ቦታ በሕገወጥ መንገድ አጥረው ቤት የገነቡበት በመሆኑ፣ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ ይዞ በመገኘትና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ባለሰደፍ አንድ ክላሽ፣ ስታር ሽጉጥና አንድ የጭስ ቦምብ ያለፈቃድ ይዘው በመገኘታቸው ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸውም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አክሏል፡፡
በክስ መዝገቡ በተካተቱ 24 ተከሳሾች ላይ ዝርዝር ተደጋጋሚ ክሶች በተናጠልና በጋራ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ አቅርቧል፡፡ 
ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. መሥርቻለሁ ያለውን ክስ ከ40 ቀናት ቆይታ በኋላ ጥቅምት 11 እና 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት አቅርቦ ያሰማው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ፣ ባቀረበው ክስ ላይ ከተከሳሾች ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ የተቃውሞው ምክንያትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ (20) ንዑስ አንቀጽ (4) መሠረት አንድ ተከሳሽ ክስ ሲመሠረትበት፣ ክሱና የማስረጃ ዝርዝር አብሮ እንዲሰጠው የተደነገገው ሕገ መንግሥታዊ መብት በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ተሟልቶ ባለመቅረቡ ነው፡፡ በመሆኑም የተከሳሽ ጠበቆች ከፍተኛ ተቃውሞ በማቅረብ በዕለቱ እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌላው ያነሱት ጥያቄ የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸው ነው፡፡ ተጠርጣሪዎች በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ፍርድ ቤት የወሰነውን ትዕዛዝ በመተላለፍ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ወደ ፖሊስ ማቆያ ቦታ መወሰዳቸውን በመግለጽም ጠበቆች ተቃውመዋል፡፡ 
ሌላው በራሳቸው ጠበቆች ባይሆንም በአቶ ከተማ ከበደ ጠበቃ የተነሳው ተቃውሞ፣ የአቶ መላኩ ፈንታን ጉዳይ ማየት የሚችለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንጂ የሁለተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አለመሆኑን በመጥቀስ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ በጠበቆች አስተያየት ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ሲያዘው፣ የማስረጃ ሰነድ ያላያያዘው ከቅድመ ክስ መግለጫ ጋር የሚቀርብ መስሎት በሌላ ቀጠሮ ለማቅረብ መሆኑን አስረድቷል፡፡ የዋስትና መብት ጥያቄን በሚመለከት የአብዛኛዎቹ ክስ ከአሥር ዓመት በላይ የሚያሳስር አንቀጽ መጠቀሱን ጠቁሞ፣ ዋስትና እንደሚከለክል ተናግሯል፡፡ የሦስት ተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄም እንደማይቃወም ገልጾ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠውም ብይን ጠበቆች ያነሱት ከክሱ ጋር የሰነድ ማስረጃ መቅረብ እንደነበረበትና ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመጠቆም፣ እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲያቀርብ አዟል፡፡ ዋስትናን በሚመለከት ተጠርጣሪ ተከሳሾች አቶ ሰመረ ንጉሤ፣ አቶ ማርሸት ተስፋዬና አቶ ዳዊት መኮንን እያንዳንዳቸው 15 ሺሕ ብር አስይዘው እንዲለቀቁ አዟል፡፡ በማረሚያ ቤት ይቆዩ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ ለጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በአቶ መላኩ ፈንታ የፍርድ ቤት የሥልጣን ጉዳይ ምላሽ ሳይሰጥ ፍርድ ቤቱ አልፎታል፡፡ የዋስትና መብት የጠየቁ ተከሳሾች ቢኖሩም፣ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክል በመግለጽ አልፎታል፡፡    
በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ ያልተያዙ ተከሳሾችን የኮሚሽኑ ሰርቪላንስ ድጋፍ ሰጭ ቡድን በቁጥጥር ሥር አውሎ እንዲያቀርባቸው አዟል፡፡ እስከ መስከረም 2006 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅባቸው የነበሩት የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ ምሕረት አብርሃም ላይ ግብር ባለመክፈል ወንጀልና የተሳሳተ ሰነድ በማቅረብ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

Source, Reporter

No comments:

Post a Comment