ጥቅምት ፳፪(ሃያ ሁለት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አባላቱን እየገመገ ሲሆን፣ ግምገማው በእርስ በርስ ሽኩቻና መጠላላፍ እየተካሄደ ነው።
ከድርጅቱ አመራሮች መካከል አንዱ ለኢሳት እንደገለጹት ድርጅቱ ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል።የዝምድና አሰራር እንዲሁም በቡድን ተደራጅቶ አንዱ ሌላውን የሚያጠቃበት ሁኔታ በሰሞኑ ግምገማ በስፋት የታየ ሲሆን፣ አብዛኛው ከታች እስከ ላይ ያለው አመራር በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ አንዱ ሌላውን እንደማያከብር ገልጸዋል።
ድርጅቱ የሚያካሂደው ግምገማ የይስሙላ መሆኑን የሚናገሩት አመራሩ፣ ከፍተኛው አመራር ሳይቀር በሙስና የተዘፈቀ ፣ በቡድን የተደራጀና ጥንካሬ የሌለው በመሆኑ ፣ ታች ያሉትን የድርጅቱ አባላትን ለመገምገም የሞራል ጉልበት አጥቷል ብለዋል።
ኦህዴድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዳክሞ ይገኛል የሚሉት አመራሩ፣ ከድርጅቱ መዳከም ጋር ተያይዞ በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው የአመራር ክፍተት በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው
አባላቱ ድርጅታቸው በመጪው ምርጫ በኦሮሚያ ክልል ያለምንም ችግር የሚያሸንፍበትን አሰራር ለመቀየስ ውይይት አካሂደዋል። ምንም እንኳ ድርጅቱ ምርጫውን በተለያዩ መንገዶች እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ቢሆንም፣ በኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው መጠላለፍ ገዢው ፓርቲ ምርጫውን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ለማስኬድ ሊከብደው ይችላል ብለዋል አመራሩ።
በኦህዴድ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዋናዎቹ የኢህአዴግ ድርጅቶች ማለትም በህወሀት እና በብአዴን ውስጥም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ጠቁመዋል።