ለልማት የሚከፈለው መስዋዕትነት በ“ደብል ዲጂት” መቀነስ አለበት!
ልማትና ትዕግስት ያላቸው ቁርኝት ዘንድሮ ገባኝ!
ልማትና ትዕግስት ያላቸው ቁርኝት ዘንድሮ ገባኝ!
እኔ የምለው … ባለፈው እሁድ ብሄራዊ ቡድናችን ብሔራዊ ኩራት አጐናፀፈን አይደል! (የልማት ውጤት እኮ ነው!) እውነቴን ነው የምላችሁ… ዋልያዎቹ ብርቅዬነታቸውን ለዓለም አሳይተዋል። በቴክኒክ ችግር 2ለ1 በሆነ ውጤት ቢሸነፍም እንዳሸነፈ እንቆጥረዋለን፡፡ የደጋፊውንም የጨዋነት ብቃት ሳናደንቅ አናልፍም፡፡ አንዳንድ ደጋፊዎች ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የ “ማሪዋና” ቅጠል የታተመበት ባንዲራ ጭንቅላታቸው ላይ ሸብ አድርገው ታይተዋል-በኢቴቪ መስኮት ሳይቀር፡፡ (ይሄኔ ነው መሸሽ) አንዳንዶች ምን ቢሉ ጥሩ ነው? የአባባ ጃንሆይ ባንዲራ (የሞአንበሳ ምስል ያለበት) ማረን ብለዋል (ማስጠየቁ ባይቀርም) አሁንም ከስቴዲየም ወጥተን ፓርላማ እንግባ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በአዲሱ ፕሬዚዳንት ንግግር ላይ ለፓርላማ የሰጡትን ማብራሪያ ተከታትላችኋል? ንዴት የማይነካቸው ጠ/ሚኒስትር ሰጥቶናል እንጂ በፓርላማ የመድረክ ተወካይ ስንት ጭርጭርር….የሚያደርግ ውንጀላ ሰንዝረዋል - በጠ/ሚኒስትሩ ላይ ሳይሆን በመንግስትና በኢህአዴግ ላይ፡፡ ዳያስፖራው በ40/60 የመንግስት ቤቶች ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆን የተደረገው፣ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብና ዳያስፖራውን በአባልነት ለመያዝ ነው ሲሉ አቶ ግርማ የወንጀሉ ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ ግን ተረጋግተው ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኢህአዴግ ከዳያስፖራው ድምፅ (የምርጫ ማለታቸው ነው) አያገኝም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከዳያስፖራ የገንዘብ ድጋፍ ተቀብሎ እንደማያውቅም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ (ኢህአዴግ እኮ ቀጭን ጌታ ነው!)
ይሄ ደግሞ እውነት መሆኑን ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ እንዴ 7 ሚ. አባላት ያቀፈ ግዙፍ ፓርቲ ለምን ብሎ ከዳያስፖራ
ገንዘብ ይለምናል፡፡ (በደህና ቀን ተቃዋሚ ፓርቲ ከመሆን ወጥቷል!) በዚያ ላይ በሽ የቢዝነስ ተቋማት አሉት
(“ኢንዶውመንት” ነው የሚላቸው?) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ራሱን “አውራ ፓርቲ” ቢልም እኮ ያምርበታል፡፡ ትልቅ
ሥልጣን (Power) ብቻ ሳይሆን ትልቅ ካፒታልም ያለው ፓርቲ እኮ ነው! እኔ ተቃዋሚ ፓርቲ ብሆን ኖሮ “ህልምህ
ምንድነው? ስባል ምን እንደምል ታውቃላችሁ? “ህልሜ ኢህአዴግን መሆን ነው!” ባይናገሩትም እኮ የሁሉም ተቃዋሚ
ፓርቲዎች ህልም ይሄው ነው፡፡ “ወፈ ሰማይ አባላት” ያሉት ገዢ ፓርቲ መሆን! ወዳጆቼ… “ህዝቡን የስልጣን ባለቤት
ማድረግ” ምናምን… የሚለው የተበላ ዕቁብ ነው!!
በ2000 ዓ.ም የኢህአዴግ ካፒታል ከ1200ሚሊዮን ብር በላይ ነበር አሉ፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) እኔ የምላችሁ … ከአነስተኛና ጥቃቅን የብድር ተቋማት፣ ገንዘብ ተበድረው ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ወጣቶች እንዳሉ ሰምታችኋል? የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ፓርላማ ውስጥ ሲናገሩ ሰምቼ እኮ ነው፡፡
ለነገሩ ጠ/ሚኒስትሩም ቢሆኑ ለማስተባበል አልሞከሩም፡፡ “ከስንዴ መሃል እንዳክርዳድ አይጠፋም” ዓይነት መልስ ነው የሰጡት፡፡ መፍትሄውም ስንዴውን ሁሉ መድፋት ሳይሆን እንክርዳዱን ለቅሞ ማውጣት ነው ብለዋል - የተከበሩ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፡፡
በ2000 ዓ.ም የኢህአዴግ ካፒታል ከ1200ሚሊዮን ብር በላይ ነበር አሉ፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) እኔ የምላችሁ … ከአነስተኛና ጥቃቅን የብድር ተቋማት፣ ገንዘብ ተበድረው ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ወጣቶች እንዳሉ ሰምታችኋል? የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ፓርላማ ውስጥ ሲናገሩ ሰምቼ እኮ ነው፡፡
ለነገሩ ጠ/ሚኒስትሩም ቢሆኑ ለማስተባበል አልሞከሩም፡፡ “ከስንዴ መሃል እንዳክርዳድ አይጠፋም” ዓይነት መልስ ነው የሰጡት፡፡ መፍትሄውም ስንዴውን ሁሉ መድፋት ሳይሆን እንክርዳዱን ለቅሞ ማውጣት ነው ብለዋል - የተከበሩ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፡፡
በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ተቃዋሚዎችና መንግስት ዓይን ያወጣ የእርስ በርስ መፈራረጅ አቁመው፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሚያግባባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት አለባቸው ሲሉም አቋማቸውን ገልፀው ነበር (የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ምክር ትዝ አለኝ!) ጠ/ሚኒስትሩ ግን ይሄ የተዋጠላቸው አይመስሉም። በእርግጥ “የተቃዋሚዎች መኖር ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል” በማለት ነው መልስ መስጠት የጀመሩት፡፡ ከዚያ ግን አመረሩ (ፊታቸው ላይ ምሬት ባይታይም!) “ሌት ተቀን የጐዳና ላይ ነውጥ አድርጌ መንግስት እለውጣለሁ” ከሚል ተቃዋሚ ጋር እንዴት ነው በጋራ መስራት የምንችለው?” በማለት ምላሽ ሰጡ፤ ጠ/ሚኒስትሩ። እኔ የምላችሁ ግን… “ነውጥ” ከ97ቱ ምርጫ ጋር “ታሪክ” አልሆነም እንዴ? እኔ እኮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ፤ ህጋዊና ሰላማዊ ይመስለኝ ነበር። ደግሞም አይፈረድብኝም … ህጋዊ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ አላቸው፡፡ ፖሊስ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ እንዴት “ነውጠኞች” ብዬ ልጠርጥር?
መንግስት ባለሃብቱን ሁሉ “ኪራይ ሰብሳቢ” ይላል በሚል ለቀረበው ውንጀላ መልስ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚለውን ቃል በትክክል ካለመረዳት የመጣ ስህተት ነው ብለዋል- በሰሞኑ የፓርላማ ውይይት፡፡ በ”ነውጥ” ጉዳይ ላይም ብዥታ (የኢህአዴግን ቋንቋ ተውሼ ነው!) ያለ ይመስለኛል፡፡
እናላችሁ … በሰላማዊ ሰልፍና በነውጥ መካከል ስላለው ልዩነት ጥልቅ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ዎርክሾፕ ነገር ያስፈልገናል፡፡ (ለእኛም፣ ለኢህአዴግም፣ ለተቃዋሚም)
በቀደም በፓርላማ ጠ/ሚኒስትሩ፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለ10 ተከታታይ ዓመት በሁለት ዲጂት ማደጉን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ (ኒዮሊበራሎችም በግዳቸው አምነዋል!) አሁን የእኔ ጥያቄ ምን መሰላችሁ? የአገሪቱ ዲሞክራሲ ማደግና መውደቁን የሚነግረን ማነው? የሚል ነው፡፡ (በዲጂት ማለቴ ነው!) ከምሬ ነው… ዲሞክራሲያችን በስንት ዲጂት እንዳደገ እንዲነገረን እንፈልጋለን። (እንደኢኮኖሚው ባለሁለት ዲጂት አስመዝግቦ ይሆናል እኮ!) ነገሩን እኛ ሳናውቀው ቀርተን እኮ አይደለም፡፡ ለወዳጅም ለጠላትም ግን በፐርሰንት ተሰልቶ ሲነገር ደስ ይላል። (ዲሞክራሲ በፐርሰንት ይለካል እንዴ?)
መቼም ጉዳችን አያልቅም አይደል? የመብራት፣ የውሃ፣ የኔትዎርክ፣ የታክሲ መጥፋት ወዘተ… አንሶን ሰሞኑን ደግሞ የዳቦ እጥረት ተከስቷል - በስንዴ መጥፋት፡፡ እናላችሁ… ሌላ የዳቦ ሰልፍ እንዳይጀመር ክፉኛ ሰግቻለሁ፡፡ (እንደታክሲው!)
Daily Express የተባለው ጋዜጣ April 17 ቀን 1933 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ፤ በሶቭየት ህብረት በአንድ አርብ ቀን ብቻ 7ሺ ሩሲያውያን ለዳቦ ተሰልፈው እንደነበር ጽፏል፡፡ (ሰልፍና ሶሻሊዝም ተለያይተው አያውቁም!) እናላችሁ… ከእንዲህ ዓይነቱ መዓት እንዲሰውረን ሱባኤ መግባት ሳይኖርብን አይቀርም። (ሱባኤ ለመግባት የግድ 7ሺ ሰው ለዳቦ መሰለፍ አለበት እንዴ?)
ባለፈው ሳምንት የገጠመኝን ደግሞ ላውጋችሁ፡፡ እንደአጋጣሚ ካዛንቺስ አካባቢ መብራት ስላልጠፋ (አንዲት ማታ እኮ ነው!) ኢቴቪ በትራንስፖርት እጥረት ዙሪያ የሰራውን ዘገባ እየኮመኮምኩ ነበር። መፍትሔ ይመጣል የሚል ተስፋ አድሮብኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሥራ ከምፈታ ብዬ ነው፡፡ የዛን ዕለት ማታና አንድ ሌላ ቀን ሁለት የካድሬ ቅላፄ ያላቸው የታክሲ ተራ አስከባሪዎች የሰጡት ድፍረት የተሞላበት አስተያየት ግርም ብሎኛል፡፡ ሁለቱም ሴቶች ናቸው፡፡
ሁለቱም ከአፋቸው ነጠቅ ነጠቅ ያደርጋቸዋል፡፡ ሁለቱም እየተቆጡ ነው የሚናገሩት። ተራ የማስከበር ሥራ ሳይሆን
የአዲስ አበባን ነዋሪ ሥነምግባር የማስተማር ሃላፊነት የተጣለባቸው ይመስላሉ፡፡ በስራ ሰዓት መግቢያና መውጪያ ላይ
ስለሚፈጠረው የትራንስፖርት እጥረት ነበር የሚናገሩት፡፡ “ህዝቡ…ቅጥቅጦች ላይ አይሳፈርም…ሁሉም ቆሞ ሚኒባስ
(ታክሲ) ነው የሚጠብቀው፤ ይሄ ተገቢ አይደለም” አሉ፡፡ ወቀሳቸው አላበቃም “ህብረተሰቡ ለምን ማልዶ ተነስቶ ወደ
ስራው አይሄድም? ሁሉም 2 ሰዓት ስለሚመጣ እኮ ነው ችግር የሚፈጠረው” አሁንም በቁጣ! አንደኛዋ ይባስ ብላ፣ል
ሰራተኛው ጠዋት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ስራ እንዲገባ፣ ማታም እንዲሁ ከስራው አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ እንዲወጣ
በፓርላማ ያልፀደቀ መመሪያ አወጣችልን፡፡
ለታክሲዎች እያቆራረጡ መጫንና ለታሪፍ ጭማሪም ተጠያቂው ህብረተሰቡ ነው ስትል ደመደመች፡፡ (አዲስ አበቤ ፈረደበት!) “ህዝቡ ራሱ እኮ ነው፤ መብቱን አያስከብርም!” አለች - ብላ፡፡
ለታክሲዎች እያቆራረጡ መጫንና ለታሪፍ ጭማሪም ተጠያቂው ህብረተሰቡ ነው ስትል ደመደመች፡፡ (አዲስ አበቤ ፈረደበት!) “ህዝቡ ራሱ እኮ ነው፤ መብቱን አያስከብርም!” አለች - ብላ፡፡
ይሄኔ አንድ ነገር ተጠራጠርኩ፡፡ ተራ አስከባሪዋ “ፒፕሉ” ላይ ቂም ሳይኖራት አይቀርም፡፡ ወይም ደግሞ “ይሄን ህዝብ ውረጂበት!” ብሎ የላካት “የውጭ ኃይል” አለ - አልኩ ለራሴ፡፡ በኋላ ላይ “እንተዋወቃለን እንዴ?” ልላት ሁላ ዳድቶኝ ነበር -በአካል አጠገቤ ያለች መስላኝ፡፡ የምትናገረው በኢቴቪ መስኮት መሆኑ ትዝ ሲለኝ በራሴ ላይ ከት ብዬ ሳቅሁኝ፡፡ (በራስ መሳቅ ጤንነት ነው ተብሏል!)
አይገርምም…በትራንስፖርት እጥረት ጠዋት ማታ የምንሰቃየው አንሶ ቤታችን ድረስ በኢቴቪ በኩል እየመጡ እንዲሁ ሲሞልጩን! ወደዘገባው መቋጫ ላይ ጋዜጠኛው ያነጋገራቸው የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ትንሽ ይሻላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለልማት የከፈለውን መስዋዕትነትና ታጋሽነት አድንቀዋል፡፡ (ሃበሻ እኮ በትዕግስት አይታማም!) የትራንስፖርት ችግሩን በተመለከተ ግን አንዳችም የመፍትሔ ሃሳብ አልሰነዘሩም፡፡ “በትዕግስታችሁ ግፉበት!” ከማለት በቀር፡፡
በነገራችሁ ላይ ልማትና ትዕግስት ያላቸውን ተፈጥሮአዊ ቁርኝት በደንብ የተረዳሁት ዘንድሮ ነው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን እዚህች መዲናችን ላይ ለልማት የሚከፈለው መስዋዕትነት ልኩን ያለፈ ይመስለኛል፡፡ (ግን መስዋዕትነት ያስፈልጋል እንዴ?) አያችሁ… አንዳንዱ መስዋዕትነት ለመንግስት ሹመኞች ስንፈት የምንከፍለው ነው። ሁሉም እየተነሳ ችግሩንና ድክመቱን በልማቱ ሲያሳብብ አያበግንም?
የሰለጠኑት አገራት እኮ እንኳን ለልማት ለጦርነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመቀነስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሰው አልባ ተዋጊ ጄቶችን ለምን የፈጠሩ ይመስላችኋል? መስዋዕትነትን በ “ደብል ዲጂት” ለመቀነስ እኮ ነው! እኛም የልማት መስዋዕትነታችንን በ “ደብል ዲጂት” መቀነስ አለብን!! (ሞትን እኮ!)