-ፓርላማው መንግሥትን እንዲቆጣጠር ጠየቁ
-አፈ ጉባዔ አባዱላ ፓርላማው እንደማያወላዳ ጠቆሙ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ የአስፈጻሚውን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ጠርቶ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት ብቸኛው አውራ ፓርቲ ለመሆን መገደዱን ገለጹ፡፡
በዚህም የተነሳ ገዢው ፓርቲ ድርብ ኃላፊነት እንደወደቀበትና ይህንን ኃላፊነትም በአግባቡ ከመወጣት ባሻገር አማራጭ ባለመኖሩ ፓርቲው የመሠረተው መንግሥት በርካታ ሥራ ተደቅኖበታል ብለዋል፡፡ ይህንንም ኃላፊነት ለመወጣት አስፈጻሚ አካላት ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ በመሆን ሥራቸውን ለሕዝቡ ግልጽ ማድረግ አለባቸው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ በመሆኑም የመንግሥትን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ሥልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል በአስፈጻሚው መንግሥት ላይ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ፓርላማው በተጠናቀቀው 2005 ዓ.ም. ግርምትን የጫረ ቁጥጥርና ክትትል በአስፈጻሚው መንግሥት ላይ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በተጠቀሰው ዓመት ለፓርላማው የቀረበው የዋናው ኦዲተር ሪፖርት መንግሥት በ2004 ዓ.ም. ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለብክነት መዳረጉንና ለምን ዓላማ እንደዋለ ማወቅ አለመቻሉን ገልጾ ነበር፡፡ ዋናው ኦዲተር ያቀረበው ሪፖርት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዓመታት የተለየ ባይሆንም ፓርላማው ግን የተለየ ትኩረት በመስጠት ግድፈት ፈጽመዋል የተባሉ ተቋማት ኃላፊዎችን በመጥራት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
በዓመቱ መጨረሻ ላይ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የቀረበውን የ2006 በጀት መመልከት ሲጀምርም ተመሳሳይ ማሳሳቢያ በመስጠት በጀቱን በአግባቡ የማይተገብሩ መሥሪያ ቤቶችን ባለመቆጣጠር ሚኒስቴሩን ተጠያቂ እንደሚያደርግ አጥብቆ መግለጹ፣ ዋና ከተባሉት አስገራሚና ድንገተኛ የፓርላማው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው፡፡
ፓርላማው ባለፈው ዓመት ያደረገውን ጠንካራ ቁጥጥር ከመጀመሩ በፊት በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንዳደረገው፣ አስፈጻሚውን መንግሥት በመሰብሰብ የተለየ ቁጥጥር ለማድረግ መነሳቱን አስታውቆ ነበር፡፡
ባለፈው ሐሙስ የተደረገውም ስብሰባ የዚሁ አካል እንደሆነ በውይይቱ ላይ የተገኙ የምክር ቤት አባላት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ፓርላማው አስፈጻሚውን ከመጥራቱ በፊት ለአምስት ቀናት በራሱ ቅጥር ግቢ ዝግ ስብሰባ ማድረጉን የገለጹት ምንጮች፣ ዘንድሮ ከተለመደው የቁጥጥርና የክትትል ሥራ የተለየ አሠራር ለመፍጠርና ተግባራዊ ለማድረግ እንደወሰነ አስረድተዋል፡፡
ፓርላማው መንግሥትን የሚቆጣጠርበትና የተለመደ የተባለው አሠራር የአስፈጻሚው መንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች በዓመት ውስጥ ቢበዛ ሁለት ጊዜ ለፓርላማው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው፡፡
ፓርላማው ዘንድሮ እንደ አዲስ ለመተግበር ያቀደው የቁጥጥርና ክትትል አሠራር ግን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን የማዳመጥ ትኩረት እንደማይኖረው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በርካታ ገጾችን የያዙ እርባና የሌላቸው ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ከማዳመጥ ይልቅ፣ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች ለይተው በሚያቀርቧቸው አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተቋማት ኃላፊዎች ሪፖርት እንዲያደርጉና ፓርላማውም በማስረጃ ላይ የተደገፈ ክርክር ውስጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ይህንን የፓርላማውን አሠራር ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ላለበት ሕግ አስፈጻሚው ለማስተዋወቅ በምክር ቤቱ በተጠራው ስብሰባ ላይም ይፋ መደረጉን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ስብሰባው እንዲከፍቱ የተጋበዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ፓርላማው በአስፈጻሚው ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባው ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም ከጀመረው አሠራር በላቀ ሁኔታ ቁጥጥር ማድረግ ቢችል ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ግንባታ ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ባለመወጣታቸው፣ ገዥው ፓርቲ ብቸኛ አውራ ፓርቲ በመሆን ድርብ ኃላፊነቶችን ለመሸከም ተገዷል፤›› ማለታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት ምንጮች ገልጸዋል፡፡
‹‹የአገሪቱ ሕዝቦች በአሁኑ ወቅት ሌላ አማራጭ ፓርቲ የላቸውም፤›› በማለት በንግግራቸው የቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የወደቀብንን ኃላፊነት ለመወጣት አስፈጻሚው መንግሥት ለሕገ መንግሥቱና ለሕዝቦች ታማኝ በመሆን፣ እንዲሁም እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል፤›› ማለታቸውን ምንጮች አክለዋል፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካላት የሚያወጧቸው መመርያዎችና ደንቦች ፓርላማው ከሚያወጣቸው ሕጎች ጋር እንዳይጣረሱ መጠንቀቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ፓርላማው የማያወላዳ ቁጥጥር በአስፈጻሚው ላይ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ የአስፈጻሚው መንግሥት ኃላፊዎች ከወዲሁ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
SOURCE, REPORTER
No comments:
Post a Comment