የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥትን ለመቃወም ሠልፍ የወጡና ፖሊስ ተጋጩ
-ቁጥራቸው ያልታወቀ የሠልፉ ተሳታፊዎች ታስረዋል
-መንግሥት ሕገወጥ ሠልፍ በመሆኑ እንዲበተን ተደርጓል አለ
በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው የግድያ፣ የድብደባና የማንገላታት ድርጊት ያበሳጫቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ ኅዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ በማምራት ላይ እያሉ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተጋጩ፡፡ ፈቃድ ያልተጠየቀበት ሕገወጥ ሠልፍ በመሆኑ በፖሊስ ለመበተን እንደተገደደ መንግሥት አስታውቋል፡፡
ሠልፈኞቹ በወሎ ሠፈር አድርገው የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ከሚገኝበት ከአይቤክስ ሆቴል ወረድ ብሎ በስተግራ በኩል ሲደርሱ፣ ፖሊስ ሠልፉ ሕገወጥ እንደሆነ በመግለጽ እንዲበተኑ ሲጠይቃቸው በተፈጠረ አለመግባባት ድብደባና መንገላታት እንደደረሰባቸው ሠልፈኞቹ ተናግረዋል፡፡
‹‹የአገራችን ዜጐች በሳዑዲ ዓረቢያ እየተገደሉና እየተሰቃዩ ስላሉ ያንን ለመቃወም ወጣን፡፡ የአገራችን ፖሊስ ለምን ይደበድበናል? ምን አደረግን?›› በማለት የሚጠይቁት ሠልፈኞቹ፣ መንግሥት የሳዑዲ ዓረቢያን መንግሥት ድርጊት ለመሸፈን ካልፈለገ በስተቀር፣ በዜጐቹ ላይ እንደዚህ ያለ ድብደባና ወከባ መፈጸም አልነበረበትም ብለዋል፡፡
ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች በተሳተፉበት የተቃውሞ ሠልፍ ውስጥ የተገኘው አንድ የሰማያዊ ፓርቲ አባል እንደተናገረው፣ መንግሥት እንኳን ያረጋገጠው ሦስት ዜጐቻችን ተገድለዋል፡፡ 23 ሺሕ ዜጐች ደግሞ ባዶ እጃቸውን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው፡፡ ይህና ሌሎች ስቃዮች እየደረሱባቸው ለሚገኙ ዜጐች በሰላማዊ ሠልፍ ተቃውሞ ማቅረብ ሊያስመታና ሊያሳስር እንደማይገባ ተናግሯል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ሠልፈኞቹ ፈቃድ ሳይጠይቁ መሠለፋቸው አግባብ አይደለም፡፡ ክልክልም ነው ብለዋል፡፡
ለሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድ ከሚሰጠው አካል ፈቃድ ሳያገኙ ሠልፍ መውጣት ሕገወጥነት ነው፡፡ ከሠልፈኞቹ ጋር ተደባልቀው የወጡ ፀረ ዓረብ ቅስቀሳ የሚያካሂዱ ተሠላፊዎችም እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው አሉ፡፡ ፖሊስ የያዛቸውም ሠልፉ ሕገወጥ በመሆኑ ነው፡፡ የሠልፉ አቀናባሪዎች በሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ምን ያህል እንደሆኑ አልታወቀም፡፡
SOURCE, REPORTER
No comments:
Post a Comment