Friday, October 11, 2013

ድሆችን ያፈናቀለው “ኢንቨስትመንት” ዕዳ ዋጠው


"እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልሸጥነው መሬት ነው" መለስ
DSCN0291


“መሬታችንን ለምን እንነጠቃለን?” በማለት የጠየቁ ተገድለዋል። ተገርፈዋል። ታስረዋል። አሁን ድረስ እስር ላይ የሚገኙ አሉ። ባዕድ እንኳን ባልሞከረው የከፋ ጭካኔ በከባድ መሳሪያ በተደገፈ የጦር ሃይል የተወለዱበትን መሬት እንዲለቁ የተገደዱ አዛውንቶች ላይ የተፈጸመው ግፍ እስከ ወዲያኛው የሚያሽር አይደለም። በሌሊት እርቃናቸውን ከሚያርፉበት ታዛ ስር ነፍጠኛ ሰራዊት እንዲከባቸው እየተደረገ የተፈጸመው አስነዋሪ ግፍ ጊዜ የሚጠብቅ እንደሆነ በየጊዜው የሚገለጽ ነው።
“የዘራሁትን ሳላነሳ በዶዘር ማሳዬን ጠረጉት፣ በዶዘር እርሻዬ ውስጥ ገብተው አረሱት፣ መሬቴን ለምን ትወስዳላችሁ? የት ልትወስዱኝ ነው? ያሸተውን በቆሎዬን መነጠሩት። ምን ላደርግ እችላለሁ። መሳሪያ የያዙ ወታደሮች ከበውኛል፣ ጠዋት ስነሳ ማሳዬ ባዶ ሆኖ አገኘሁት … ” ይህ ሁሉ የበደል ሰቆቃ ነው። በምስል ተደግፎ የቀረበ ህሊናን የሚሰብር መረጃዎች አሉ።
anuak man
(Photo: IC magazine)
አንድ የአካባቢው ነዋሪ “ሰላማዊ ህዝብ፣ በቅጡ የሚለብሰው እንኳን የሌለውን ህዝብ፣ አሮጊቶችን፣ አዛውንቶችንና ህጻናትን ሲገድሉና ሲያሰቃዩ የቆዩት ለዚህ ነው? ለዚህ ኢንቨስትመንት ነው ያ ሁሉ የተፈጥሮ ደን ወድሞ ከሰል እንዲሁን የተደረገው? ገንዘብ ሳይሆን የከሰል ጆንያ ይዘው ክልሉን እንዲቀራመቱ የሚፈቅዱት ክፍሎች ስለጊዜና ስለዘመን ለምን አያስቡም?” ሲል ይጠይቃል። በማያያዝም “70 ከመቶ የሚሆኑት ባለሃብቶች የትግራይ ሰዎች መሆናቸውን እናውቃለን። መረጃውም አለን። እባካችሁ የተጨቆናችሁ የትግራይ ወንድምና እህቶች እባካችሁን በስማችሁ እየተፈጸመብን ያለውን በደል ተቃወሙ” ሲል ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ አስረድቷል።
አዛውንቱ ጸሐይ ለመሞቅ ታዛ ስር ቁጭ ባሉበት (በፎቶው የሚታዩት አይደሉም) ከሙሉ ቤተሰባቸው ጋር የጥይት ራት የተደረጉበት ኢንቨስትመንት አስቀድሞ የተገለጸ ቢሆንም መጨረሻው ሌብነት እንደሆነ ኢህአዴግና ራሱ ድርጅቱ ማመናቸው ተሰማ። አቶ መለስ ሲጀነኑበት የነበረው ኢንቨስትመንት አውላላ ሜዳ ላይ የተደፋ ስለመሆኑ የተጠየቁት አቶ ኦባንግ ሜቶ “እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልተሸጠው መሬት ነው” በማለት አቶ መለስ የተናገሩትን በማስታወስ “ህዝብን የማይሰማ ድርጅት ዞሮ ዞሮ ከውርደት አይድንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የሰሙት ዜና የሚጠበቅ እንደሆነ ያመለከቱት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ “ሚዲያዎች በነካ እጃቸው ስለ ሰለባዎቹም ይተንፍሱ” ሲሉ ጠይቀዋል።
የሰንደቅ ዜና እንዲህ ይነበባል፡

የህንድ ካራቱሪ ኩባንያ 62 ሚሊዮን ብር የንግድ ባንክን ዕዳን መክፈል አልቻለም

  • ኩባንያው የሠራተኞች ግብር፣ ጡረታ እንዲሁም የክልሉን የመሬት ግብር አልከፈለም
  • ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸውን ማሽነሪዎች በማከራየትና በመሸጥ እየተከሰሰ ነው።
  • ከተረከበው 300 ሺ ሔክታር ያለማው 800 ሔክታር ብቻ ነው።
መሠረቱን በጋምቤላ ክልል ያደረገው የህንድ ካራቱሪ አግሮ ፕሮዳክት ኀ/የተ/የግ/ማህበር በተሰጠው መሬት ላይ የልማት ሥራ ማከናወን አለመቻሉን እንዲሁም የባንክ ብድርና የግብር ግዴታዎቹን እየተወጣ አለመሆኑ ተገለፀ።
አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ የቢዝነስ ዴቭሎፕመንት የስራ ሒደት ባለቤት ስለጉዳዩ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዳስረዱት “ካራቱሪ ከባንኩ እ.ኤ.አ በዲሴምበር 2011 ወደ 62 ሚሊየን ብር ብድር መውሰዱን አስታውሰው ነገር ግን መክፈል በሚገባው ጊዜ ሊከፍል አለመቻሉን፣ ብድሩንም ለማስታመም የተደረጉ ተጨማሪ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ጉዳዩ ወደህግ ክፍል መመራቱን አስታውቀዋል። ባንኩ በአሁኑ ወቅት ይህ ብድር የተበላሸ ወይንም መመለስ የማይችል ነው በሚል ጉዳዩን ይዞት ለማስመለስ ወደ ሕጋዊ እርምጃ መግባቱን” ተናግረዋል።
በተያያዘም በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ከአራት ዓመት በፊት በጋምቤላ ክልል 300ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ተዋውሎ የገባው የህንዱ ኩባንያ ካራቱሪ ባለው ደካማ ማኔጅመንት ምክንያት ሥራውን ማከናወን ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ትልቅ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
አቶ አለምሰገድ አያሌው የኩባንያው የምርት መሳሪዎች ዋና ክፍል ኃላፊና የሠራተኞች ተወካይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በስልክ እንደገለጹት ኩባንያው 300ሺ ሄክታር ለማልማት ከግብርና ሚኒስቴር መሬት ተረክቦ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አምስት አመታት ከ800 ሄክታር በላይ ለማልማት አልቻለም።
ግብርና ሚኒስቴር ይህንኑ ደካማ አፈጻጸም በማየት ከአንድ ዓመት በፊት 200ሺ ሄክታር መሬት የነጠቃቸው መሆኑን አቶ አለምሰገድ አስታውሰው ይህንንም ማልማት ባለመቻላቸው በአሁኑ ወቅት በእጃቸው የሚገኘው መሬት 10ሺ ሄክታር ብቻ ነው ብለዋል። ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በበቆሎ ሰብል የተሸፈነው 800 ሄክታር ገደማ ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ድርጅቱ 150 ያህል ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት ያስታወሱት አቶ አለምሰገድ የሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ እስከ 45 ቀናት እንደሚዘገይ፣ ለጡረታና ለግብር ከሰራተኛው የሚሰበሰበው ክፍያ በአግባቡ ለሚመለከተው አካል እንደማይገባ ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
የኩባንያው አመራሮች በውጪ ምንዛሪ የሚያስገቡዋቸውን ዘርና ማዳበሪያ በአገር ውስጥ እንደሚሸጡ፣ ከቀረጥ ነጻ ያስገቡዋቸውን ማሽነሪዎች በማከራየትና ለሶስተኛ ወገን በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም እንደሚያጋብሱ ተናግረዋል።
ይህንኑ አቤቱታቸውን ለጋምቤላ ክልል የሚመለከታቸው መ/ቤቶች በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ጆን ሾል ስለጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው የካራቱሪ የስራ አፈጻጸም እጅግ ደካማ መሆኑን አረጋግጠዋል። ኩባንያው በተጨማሪም ለወረዳ መክፈል ያለበትን የመሬት ግብር ጭምር እንዳልከፈለ የጠቆሙት አቶ ጆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የተበደረውን ባለመክፈሉ ባንኩ በመያዥነት የያዛቸውን ንብረቶች ወደማስከበር ስራ ፊቱን ማዞሩን ጠቁመዋል።
በቅርቡ ከፌዴራል መንግስት ባለሙያዎች ወደቦታው መጥተው ችግሩን አጥንተው መመለሳቸውን ጠቁመው በቅርቡ ኩባንያውን በተመለከተ የመጨረሻ መፍትሔ ሊገኝ እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የካራቱሪ አግሮ ፕሮዳክት ኃ.የተ.የግ.ማኅበር (ጋምቤላ ኤሊያ አካባቢ) የሥራ ኃላፊዎችን በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
SOURCE, GOLGUL WEBSITE

No comments:

Post a Comment