አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ፣ የፒቲኤ ባንክ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ከሰላሳ ዓመት በላይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የቆዩና ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል፡፡
በአራት ቋንቋዎች ይናገራሉ፤ ይሠራሉ፡፡ አማርኛን ጨምሮ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ዓረብኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ በኢኮኖሚክስና በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለት የማስትሬት ዲግሪዎችንም ይዘዋል፡፡ ሐርቫድን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ዕውቀታቸውን አዳብረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ከዚያም በሻገር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አገልግለዋል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከመወለዳቸውም በሻገር በሱዳን የልጅነታቸውን ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ የቄስ ትምህርት ቤትን በካርቱም ተከታትለዋል፡፡ አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ፣ ራሳቸውን እንደሉላዊ ሰው መመልከትን ይመርጣሉ፤ የበርካታ ባሕሎችና ሕዝቦች ውጤት እንደሆኑም ያስባሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ የንግድና የልማት ባንክ የሆነውን ፒቲኤ ባንክን በፕሬዚዳንትነትና በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ባንኩ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ ያካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ እዚህ እንዲከናወን ከመነሻው ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጉት እሳቸው ናቸው፡፡ ፒቲኤ ባንክ ለኢትዮጵያ ስላሰባቸውና ስለሌሎች ተግባራቱ ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ፈርጀ ብዙ የሚያስብል የትምህርትና የቋንቋ ችሎታ አለዎት፡፡ አምና ሽልማቶችን ለማግኘት መቻልዎ ከምክንያቶቹ አንዱ ይኼው ሰብዕናዎ ይሆን?
አቶ አድማሱ፡- አዎ! አምና በጣም ዕድለኛ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡ ሁለት ሽልማቶችን ተቀብያለሁ፡፡ አንደኛው ‹‹The Up and Coming Leader of the Year›› ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ስብሰባ ወቅት እገረ መንገዳቸውን ባካሄዱት የሽልማት ሥነ ሥርዓት ወቅት የተሰጠኝ ነው፡፡ ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ ሌላኛውን ሽልማት ለመቀበል ብሥራቱ ደርሶኛል፡፡ የዓመቱ የአፍሪካ ቢዝነስ መሪ (The African Business Leader of the Year) ሽልማትን ከሌሎች ሦስት አፍሪካውያን ጋር አግኝቻለሁ፡፡ አንደኛው የቅርብ ጓደኛዬና የሥራ አጋሬ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከተሸለምነው ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ ሁላችንም ምሥራቅ አፍሪካን ወክለናል፡፡ እሳቸው ኢትዮጵያን ወክለዋል፡፡ እኔ የአፍሪካ ምስራቃዊና ደቡባዊ ክፍሎችን የሚያካልል ተቋም ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ስለዚህ ዓምና ጥሩ ዓመት ነበር ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ 2013 ከሽልማቶች ጋር ነው የጀመርነው፡፡ በኬፕ ታውን የዓመቱ የንግድና ፋይናንስ ባንክ የተሰኘውን ሽልማት አግኝተናል፡፡ ይኼም ለእኛ ተጨማሪ ትንግርት ሆኖልናል፡፡ ከባንኩ ጋር 18 ወራትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ በጣም ፈጣኑ ጊዜም ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮችን አሳክተናል፡፡ የባንኩ የቦርድ አባላትና የሥራ አጋሮቼ አብረውኝ ለመሥራት ተነሳስተው ነበር፡፡ በባንኩ ውስጥ ለመተግበር ያቀድኳቸውን አዳዲስ አስተሳሰቦች ተቀብለው ከባንኩ የአምስት ዓመት ዕቅድ ጋር ለመተግበር ፈቃዳቸው ሆኗል፡፡ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ለማምጣትና ለመተግበር ብዙ ተጉዘናል፡፡ ባንኩ አዳዲስ ዓላማዎችን በመያዝ መሀል ላይ እንደ አገናኝ ሆኖ ከማገልገል ባሻገር፣ ፈንድ በማስተዳደርና ለደንበኞቻችን ምክር በመስጠት ጭምር ለመጓዝ የሚያስችለንን ዓላማ ይዘናል፡፡ ህልሜ ሁልጊዜም በዓለም ላይ ምርጥ ተብለው ከሚጠቀሱ አንዱ የሆነ አፍሪካዊ ተቋም መፍጠር ነው፡፡ ከየትኛውም ሥፍራ ይሁን ብቻ የአፍሪካን ምርጥ ነገሮች ለማምጣት አልማለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ህልምዎ ተሳክቷል ማለት ይቻላል?
አቶ አድማሱ፡- ወደዚያው እያመራ ነው፡፡ በመስመራችን ላይ ስለምንገኝ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ዕውቀት ያካበቱና ክህሎቱ ያላቸው በርካታ አፍሪካውያን ከመላው ዓለም ወደ ባንካችን ለመምጣት ማመልከቻቸውን እየላኩ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉት መልሰው መስጠት የሚገባቸውን ነገር እንዳለ ስለተገነዘቡ ነው፡፡ ከራሳቸው ጋር የሚያዛምዱት ነገር እንዳለ ስለተሰማቸው ነው፡፡ ሉላውያን አፍሪካውያን (ግሎባል አፍሪካንስ) የሚለውን አጠራር አብዝተን እንጠቀማለን፡፡
ሪፖርተር፡- ዕድሜዎ ገና በአርባዎቹ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ዕድሜዎ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅስ ተቋም መምራትዎን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አድማሱ፡- ሁልጊዜም አንድ ዓይነት አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባኛል የሚል ግፊት ይመራኛል፡፡ ውጤቶችን በማግኘትና በማስመዝገቤ እደሰታለሁ፡፡ በማደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ልቀት መኖር እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ሳለሁ ጎበዝ ነበርኩ፡፡ በስፖርት ጎበዝ ነበርኩ፡፡ ትምህርት ቤቴን በቴኒስ ስፖርት የምወክል ጎበዝ ተፎካካሪ ነበርኩ፡፡ ሁልጊዜም ለራሴ የምችለውን ያህል ጥሩ ውጤት ለማምጣት ስተጋ ቆይቻለሁ፡፡ ይኼም ጠንክሮ በመሥራት እንድኖር አስችሎኛል፡፡ ሁልጊዜ አዳዲስና የተሻሉ ነገሮችን ለማከናወን በመሞከሬ ለልጆቼም ለአገሬም ተምሳሌት መሆን እንደቻልኩ ለመናገር እችላለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ጭምር ለዘመናት የቆዩ አሉታዊ አመለካከቶችን የመለወጥ ኃላፊነት አለብን፡፡ እናም በዓለም ምርጡን የአፍሪካ ተቋም ስለመፍጠር ስናገር፣ አፍሪካውያን እንደማንኛውም ሰው የዓለም ምርጦች ይሆናሉ የሚለው ሐሳብ ያስደስተኛል፡፡ የትምህርት ዕድሉን አግኝቶ ማንነታችንን የማሳየት ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የምመራበት ፍልስፍናዊ አመለካከቴ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የባንክዎ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ እዚህ ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ልትመረጥ ቻለች?
አቶ አድማሱ፡- ባለፈው ዓመት ከአባል አገሮች አንዱ ስብሰባውን እንዲያካሂድ ዕድል ተሰጥቶ ነበር፡፡ ከገንዘብና ኢኮኖሚል ልማት ሚኒስትሩ ጋር በነበረን ውይይት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በመሆኑና በዓሉም ዓመቱን ሙሉ የሚከበር መሆኑን በማስታወስ ጉባዔው እዚህ እንዲደረግ ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ ፒቲኤ ባንክ ፓን አፍሪካኒዝምን ከሌሎች ጋር ለመዘከር አብሮ ቢሠራና ቢያከብረው ካላፉት 50 ዓመታት ይልቅ መጪዎቹ 50 ዓመታት የተለዩ መሆናቸውን ለማሳየት ይረዳ እንደሆነ በማሰብ ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከባድ ጊዜን አሳልፈዋል፡፡ ስለዚህ የባንኩ ዓመታዊ ጉባዔ እዚህ መካሄድ የሚችልበት ዕድል መገኘቱ አስደስቶኛል፡፡ እግረ መንገዳችንንም ባንኩን ኢትዮጵያ ውስጥ በማስተዋወቅ፣ ስትራቴጂካዊ ሚና እንዳለው፣ የደጋፊነት ተግባሩንም ማሳየት ይችል ዘንድ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ለመደገፍ ባንኩ ሚና ሊኖረው እንደሚችል አጋጣሚው ጠቅሞናል፡፡ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አምስትና አሥር ዓመታት ውስጥ ስትራቴጂካዊ አጋር እንደሚያስፈልጋት አስባለሁ፡፡ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡ ሆኖም ግን አቅም መፈጠር አለበት፡፡ ከቻይና፣ ከህንድና ከቱርክ ኢንቨስትመንቶችን እየሳብን ነው፡፡ ደቡብ ኮሪያዎችም እየመጡ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም የድርሻውን እያበረከተ ነው፡፡ ሆኖም ትልቅ አገር፣ ሰፊ ሕዝብና እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ሲኖርህ የሚጠይቀውም ነገር ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ 100 ወይም 500 ሚሊዮን ዶላር ለዚህ ጥሩ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ይፋ ከተደረገው 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ባሻገር ለኢትዮጵያ የተዘጋጀ ሌላ ብድር ይኖር ይሆን?
አቶ አድማሱ፡- አምና ያፀደቅነው የ100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጅማሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ለመሥራት ይቻላል፡፡ እዚህ ከበርካታ ባለድርሻዎች ጋር ጥሩ ውይይቶችን ሳካሂድ ቆይቻለሁ፡፡ በርካታ ስኬታማ የሆኑ ድርጅቶች ስላሉ ለባንኩ ጥሩ ደንበኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ በባንኩና በመንግሥት ድርጅቶች እንዲሁም በግሉ ዘርፍ መካከል አጋርነትን ለመፍጠር እየሠራሁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለየ ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን ፒቲኤ ባንክ በጋራ ጥቅም ላይ በመንተራስ ድጋፉን ሊሰጣቸው የሚችሉ ሌሎችም አሉ፡፡ መልካሙ ነገር ደግሞ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋም ከመሆናችን ባሻገር እምነት የሚጣልብንና ተዓማኒ መሆናችን ነው፡፡ ከደንበኞቻችን ጋር አብረን በመሥራት ዓላማቸውን እንዲያሳኩ በቁርጠኝነት አብረናቸው እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከባንኩ ብድር ጠይቆ ሲፈቀድለት የአሁኑ የመጀመርያው አይደለም፡፡
አቶ አድማሱ፡- አዎ! አየር መንገዱ ከዚህ በፊትም ከባንኩ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ሆኖም በጣም በጥቂት መጠን …
ሪፖርተር፡- የ15 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዚህ ቀደም አግኝቶ ነበር?
አቶ አድማሱ፡- አዎ! አሁን ግን ከበፊቱ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ብድር አግኝቷል፡፡ ብድሩ ያን ያህል ትልቅ ነው ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ሆኖም ጅምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ድርጅቶች ውጤታማው በመሆኑ ባንኩ ልዩነት መፍጠር እንደሚችል እናምናለን፡፡ አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ቢሆንም የአፍሪካም ነው፡፡ ፓን አፍሪካዊ ተቋም ነው፡፡ ሌሎች አፍሪካዊ አየር መንገዶችን ያሠለጥናል፡፡ በጣም ተፈላጊውን አገልግሎት በመላ አኅጉሪቱ እያበረከተ የሚገኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እኮራለሁ፡፡ በዋጋውም የሚመረጥና ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ አየር መንገድ ነው፡፡ እንደሌሎች ተቋሞች ሁሉ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድም ማስተካከል የሚኖርበት ጉዳዮች አይጠፉም፡፡ ይህም ሆኖ በጥሩ አካሄድ ላይ የሚገኝ አየርመንገድ ነው፡፡ እየስተስፋፋ፣ እያደገና አትራፊም እየሆነ መጥቷል፡፡ አየር መንገዱ ጠንካራ አመራርና ጥሩ ራዕይ ያለው በመሆኑ እሱን መደገፍ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ከአክሰስ ካፒታል ሰርቪስስ ኩባንያ ጋርም ባንክዎ ግንኙነት ነበረው፡፡ ብድር በመስጠት ሒደት ላይም ነበራችሁ፡፡
አቶ አድማሱ፡- ይኼ የቆየ ነው፡፡ እነሱ ነበሩ ለእኛ የብድር ጥያቄውን ያቀረቡት፡፡ ያን ያህል እንዲጓዝና ብድሩ እንዲፈቀድ ግን አላደረግንም፡፡ ይኼ ግን እኔ ባንኩን ከመቀላቀሌ በፊት የሆነ ነው፡፡ ወደ ፒቲኤ ባንክ ከመጣሁ ሁለተኛ ዓመቴ ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ማመልከቻዎች ለባንኩ መድረሳቸውን ሰምቻለሁ፡፡ በርካታ የብድር ጥያቄ ማመልከቻዎች ከየድርጅቱ ይጎርፋሉ፡፡ ሆኖም ስለብድር ጠያቂው ተቋም የሀብት ይዘት እርግጠኛ መሆንን እመርጣለሁ፡፡ ፒቲኤ ባንክ ቢስነዝ የሚሠራው ከጠንካራ አጋሮቹ ጋር መሆኑን ማረጋገጥ አለብኝ፡፡ ብድር እንዲሰጣቸው የኋላ ታሪክ ያላቸውና ለብድር ብቁ የሆኑ ተቋማት ላይ የማተኩረውም ለዚህ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከፒቲኤ ባንክ መሥራቾች አንዷ ብትሆንም፣ ከባንኩ ያን ያህል ድጋፍ ማግኘት ያልቻለችው ለምንድን ነው?
አቶ አድማሱ፡- በፍላጎትና አቅርቦት ምክንያትም ነው፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለበርካታ ዓማታት ቆይቻለሁ …
ሪፖርተር፡- ከ30 ዓመታት በላይ?
አቶ አድማሱ፡- አዎ! ጥያቄው በእርግጥ የማዛመድ ነው፡፡ ፍላጎትን ማግኘትና ከአቅርቦት ጋር ማዛመድ ነው፡፡ ገበያውን የሚረዱ ሰዎችን ማግኘት፣ በአገር ውስጥ ልማት ተኮር የሆነ የቢዝነስ ፋይናንስን ለማንቀሳቀስ ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎችን ማግኘት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳን ለሁሉም ተቋም አይመቹም፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ቢዝነስ መሠራት ከባድ ነው፡፡ የቋንቋና የሕግ ጉዳዮች ቀላል አይደሉም፡፡ እግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑ አገሮች ውስጥ እንዳለው በኢትዮጵያና በሱዳን ውስጥ በቀላሉ ገብቶ፣ በቀላሉ ቢዝነስ መሥራት አይቻልም፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚታወቁ ናቸው፡፡ ለአብዛኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መግባት እንደሚቻል፣ እንዴት መሰማራት፣ ማንን እንዴት ማናገር እንዳለባቸውና የአገሪቱን ውስብስብ ጉዳዮች ለመረዳት ቀላል አይሆንላቸውም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሁሉን ነገር በቅጡና በአግባቡ ሁኔታውን መረዳትን የሚጠይቅ ነው ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በደንብ አውቃታለሁ፡፡ ፒቲኤ ባንክ የትኛውን ሪስክ መውሰድ እንዳለበትና እንደሌለበትም በሚገባ እገነዘባለሁ፡፡ ይኼው ግምገማ በተመሳሳይ በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎና በሌሎችም ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ እነዚህ አገሮች በቀላሉ ገራገር ልብ ላላቸው ሰዎች የሚሆኑ አይደሉም፡፡ እኔ ፍላጎቱ አለኝ፡፡ እነዚህን አገሮች የመደገፍ ሥልጣኑም አለኝ፡፡ ሆኖም ቢዝነስ በምንሠራበት ጊዜ የምርጫና የትኩረት አቅጣጫዎች ይኖራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን በሚመለከት ብድር እንዲያገኙ ቅድሚያ የተሰጣቸው መስኮች አሉ?
አቶ አድማሱ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በኤክስፖርት ዘርፉ ላይ ትልቅ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ በተለይ በቡናና በቆዳ፣ በማናቸውም የኤክስፖርት ሸቀጦች ላይ ትኩረቴን አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን ለትራንስፖርት ዘርፉም ብድር ለመስጠት እንፈልጋለን፡፡ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ልንሠራ የምንችላቸው በርካታ ተግባሮች አሉ፡፡ በቴሌኮም ዘርፉም እንዲሁ ከፍተኛ ፍላጎት አለን፡፡ በማዕድን ዘርፉም ላይ የተወሰነ ድጋፍ ለማድረግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን በዘርፉ ላይ የሚሳተፈው አካል ማንነት ይወስነዋል፡፡ ፒቲኤ የብዙኃን አካላት ተቋም እንደመሆኑ ምንም እንኳ እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት የሚኖረኝ የኃላፊነት ሚና ቢኖርም፣ ውሳኔው ግን የብዙኃኑ ነው፡፡ ባንክ እንደመሆኑም የአንድ ሰው ትዕይንት አይኖረውም፡፡ ምን ዓይነት አደጋ እንዳለ እገነዘባለሁ፡፡ የትኛው እንደሚበርና እንደማይበር አውቃለሁ፡፡ ብዙም ርቀት ሊጓዝ የማይችል ነገር ላይ በጉጉት ላለመንጠላጠል እጠነቀቃለሁ፡፡ በምሠራው ሥራ አብዝቼ ዲስፒሊን እከተላለሁ፡፡ የትም ሊደርስ በማይችል ነገር ላይ ተመርኩዤ ለመራመድ አልፈቅድም፡፡
ሪፖርተር፡- ብድር ሊሰጣቸው የሚችሉ እጃችሁ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ?
አቶ አድማሱ፡- በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሊውል የሚችል ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በእጃችን አለ፡፡ ይህ ገንዘብ በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ ለመገልገል የሚያስችል ነው፡፡ በአገሪቱ ፍላጎትና ምርጫ ላይም የሚወሰን የብድር መጠን ነው፡፡ እኛ እንደ ልማት ባንክ ወይም ደግሞ እንደ የአፍሪካ ልማት ባንክ አይደለንም፡፡ ርካሽ ገንዘብ የለንም፡፡ ከአፍሪካ ካፒታል ገንዘብ የምንሰበስብ ተቋም ነን፡፡ ከደቡብ ካፒታል ገበያዎች ገንዘብ እናሰባስባለን፡፡ ለጋሾች የሉንም፡፡ በለጋሾች ትከሻ ላይ የተመሠረትንም አይደለንም፡፡ በፕሮጀክቶች ላይ እናተኩራለን፡፡ ከእኛ በሚበደሩት ገንዘብ ጥሩ ሥራ ሠርተው፣ ገንዘብ አግኝተው ብድራቸውን የሚመልሱ ደንበኞችን እንፈልጋለን፡፡ በልግስና መልክ ገንዘብ ለመስጠት አልተቋቋምንም፡፡ ወደ ዓለም ባንክና አፍሪካ ልማት ባንክ የማቅናት ዕድሉ ነበረኝ፡፡ ወደ ፒቲኤ የመጣሁት ከፍ ወዳለ ሌላ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችለን በርካታ ጉዳይ እንዳለ በማመን ነው፡፡ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ጠንካራና የማያወላውል አቋም ያላቸው የሥራ ሰዎች ያሉበት ተቋም በመሆኑ ቢዝነሱም እንደዚያው ነው፡፡ ይኼ የፒቲኤ ባንክ መገለጫ ጠባይ ነው፡፡ ስለዚህ የምትመርጣቸው ደንበኞችና ፕሮጀክቶች ውጤታማ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆን መቻል አለበት፡፡ በርካታ የብድር ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የተቋሙ ጠባይ በመሆኑ ሳቢያ ሁሉንም ጥያቄዎች አናስተናግድም፡፡ ከ15 እና ከ20 ዓመታት በፊት ባንኩ መጥፎ ውሳኔዎች በመወሰኑ የተበላሸ ታሪክ ነበረው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የባንኩ ባለድርሻዎችና የሚመለከታቸው የባንኩ አካላት በባንኩ ‹‹ሪስክ ማኔጅመንት›› ላይ እጅግ ጥንቁቅ ናቸው፡፡ ስስ ስሜት አላቸው፡፡ 17 የባንኩ መሥራች አባላት አገሮች አሉ፡፡ በየአገሮቹ ለመበደር ትልቅ አቅም ያላቸው፣ የመንግሥት ድጋፍና ማስረጃ የያዙ ተበዳሪዎች ይመጣሉ፡፡ ባንኩ የብዙኃን በመሆኑ እነዚህ ነገሮች የብድር ጥያቄውን ወደሌላ ምዕራፍ አይወስዱትም፡፡ በዚያም ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ውሳኔ የሚሰጡ፡፡ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ማላዊና ሌሎችም አገሮች በርካታ ጥያቄዎችን እያቀረቡልን ነው፡፡ አንድን ፕሮጀክት በተናጠል እናይና በባንኩ ሊያስተናግድ የሚችል ከሆነ እንቀበለዋለን፡፡ ነገር ግን በመተማመን ላይ እንድንንጠለጠል የሚጋብዝ ሆኖ ካገኘነው በየአገሩ ላሉት ተቋማት እንተውላቸዋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ቢሯችሁን እዚህ ለመክፈት አቅዳችኋል?
አቶ አድማሱ፡- በአሁኑ ወቅት እዚህ ቢሮ ለመክፈት የሚያስችለንን ውሳኔ አልወሰንንም፡፡ አሁን ላይ ይህንን ለመናገርም ጊዜው አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ገንዘብ ድርጅት የተባለ ተቋም ለመመሥረት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የደቡባዊና ምሥራቃዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)፣ የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የልማት ማኅበረሰብ (ሳድክ) እና የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (ኢኤሲ) የሦስትዮች ጥምረት ለመመሥረት ተስማምተዋል፡፡ ይኼ ለፒቲኤ ባንክ ምን ማለት ነው?
አቶ አድማሱ፡- ይኼ ማለት ለእኛ የመስፋፋት ዕድልን የሚፈጥርልን ነው፡፡ ለሁሉም አካል ጥቅም የሚሆን ካፒታል እንድናሰባስብ ዕድሉን ይፈጥርልናል፡፡ በፋይናንስ ባህሪም የበርካታ ስብስብ ኃይል ሲኖር ጥሩ አቅም ይኖርሃል የሚል ነው፡፡ መሠረትህ ከፍተኛ ከሆነ በቋሚ ሀብቶች ላይ የምታካሂደው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ይሆንልሃል፡፡ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጥሃል፡፡ ትልቅ ዳራ ሲኖረን ጥቅማችን ትልቅ ይሆናል፡፡ ከ17 አባል አገሮች ውስጥ አምስት ያህሉ አነስተኛ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጥቂት አቅሙ ያላቸውና ኪሳቸው መግባት የምንችል ተጨማሪ አገሮች ሲኖሩ የኃይል ሚዛኑ ይመጣጠናል፡፡ ተጨማሪ ካፒታል መኖሩ ለሁሉም ጥቅም ስለሚያስገኝ፣ ተጨማሪ ቦንድ ለመሸጥና የገንዘብ ኃይላችንን ከፍተኛ ለማድረግ ይጠቅመናል፡፡ ይኼ አካሄድ ለኢንቨስተሮችም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ ኢንቨስተር ድርሻ ለመግዛት ሲፈልግ፣ ኢንቨስት በሚያደርግበት ባንክ ውስጥ እንደ ሞዛምቢክ፣ አንጎላና አልጄርያን የመሰሉ አገሮች ቢኖሩ ይመርጣል፡፡ የተትረፈረፈ የሀብት ምንጭ ያላቸው አገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ አልጄርያ በአሁኑ ወቅት የባንኩ ተጠባባቂ አባል አገር ናት፡፡ እንደ አልጄርያ ዕምቅ ካፒታል ያላትን አገር በአባልነት መያዙ ጥሩ የሚሆነው፣ ተጨማሪ ካፒታል ወደ ባንኩ ለማምጣት ስለሚያግዝ ነው፡፡ ይኼ ለሁለቱም ወገን ጥቅም የሚሰጥና ለሁሉም ወገን የሚበጅ በመሆኑ ጠቃሚ ነው፡፡ የባንኩን ደረጃ ለሚያወጡ ኤጀንሲዎችም ጥሩ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ የባንኩ ደረጃ በጨመረ ቁጥር በርካሽ ዋጋ ብዙ ካፒታል ለመጨመር ዕድል ስለሚፈጥርልን፣ የባንኩን የገንዘብ መጠን ብቻ ሳይሆን ለገንዘብ የሚወጣውን ወጪም በመቀነስ ጥቅም ይሰጠናል፡፡ በርካታ አገሮች የሚፈልጉትን የረጅም ጊዜ ብድር ለመስጠትም ዕድል ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን ጠንካራ አቅም ያላቸው ባለአክሲዮኖችን በአባልነት መያዝ ካልቻልክ፣ የሒሳብ መዝገብህም በሌሎች ሰዎች ዕይታ ጤናማ ካልሆነ፣ አቅም ያላቸውን አቅም ከሌላቸው ጋር በማዋሀድ ብዝኃነትን መፍጠር ይጠበቅብሃል፡፡
ሪፖርተር፡- በባንኩ ከፍተኛ አፈጻጸም ያላቸው ወይም ደግሞ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተጠቃሚ አገሮች የትኞቹ ናቸው?
አቶ አድማሱ፡- ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌና ማላዊ ሲሆኑ ምናልባት ኬንያ ትከተላለች፡፡ በቅርቡም ታንዛኒያ ወደላይ መጥታለች፡፡ ሱዳንም በፍጥነት በመምጣት ላይ ትገኛለች፡፡ የባንኩን ጥቅም የሚያገኙ አገሮችን ቁጥር ለመጨመር እየሞከርን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- አውደ ዓመትን እዚህ ሲያሳልፉ በአጋጣሚ ነው ወይስ አዘውትረው ወደ አገር ቤት ይመጣሉ?
አቶ አድማሱ፡- አዎን! እመጣለሁ፡፡ ባለቤቴ ያቋቋመችው ፋውንዴሽን አለን፡፡ እሷው የመሠረተችውና የምትመራው ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕፃናት ፈንድ (Ethiopian Children’s Fund) ይባላል፡፡ ከተቋቋመ ከ15 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ወጣ ብላ በምትገኘው አለልቱ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ፋውንዴሽን ነው፡፡ 600 ያህል ተማሪዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ከምንሠራውና ከምናደርገው ነገር ባለፈ ለአገራችን አንድ አስተዋጽኦ ማድረጋችንን ለመግለጽ የምንሞክርበት ነው፡፡ ማኅበራዊ ግዴታችንን በንቃት የመወጣት ኃላፊነታችንን የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ከሦስት ዓመታቸው ጀምሮ በእኛ ተቋም ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ ሕፃናት መካከል ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ይገኛሉ፡፡ ወላጆች የሌላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እናታቸውን፣ አባታቸውን ወይም ደግሞ ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ያጡ ናቸው፡፡ የድሃ ድሃ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነሱን ለመርዳት በየዓመቱ ወደዚህ እንመጣለን፡፡ እዚህ ቤት ስላለንም በየጊዜው እንመጣለን፡፡ ሳናቋርጥ የወሰድነውን ለማኅበረሰቡ መልሰን በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ፒቲኤ ባንክን የዓለም ምርጡ ባንክ ለማድረግ አስበዋል፡፡ በደረጃ አውጪዎች ከፍተኛ ነጥብ የሚሰጠው ወይም ‹‹ትሪፕል ኤ›› የሚያገኝ ባንክ ይሆናል ማለትዎ ነው?
አቶ አድማሱ፡- እንደዚያ ማለቴ አይደለም፡፡ ባንኩን ቢያንስ ወደኢንቨስትመንት ባንክነት ደረጃ ለመውሰድ ነው የምናስበው፡፡ ይህም ማለት ባለሦስት ቢ ወይም ‹‹ትሪፕል ቢ›› የሚባለውን ደረጃ እንዲይዝ ለማድረግ ነው የምንሠራው፡፡ ፒቲኤ በአሁኑ ወቅት ‹‹ደብል ቢ›› ደረጃን ይዞ የሚገኝ ባንክ ነው፡፡ በርካታ አጋሮችን ለመሳብ ችለናል፡፡ ሆኖም አሁን ባገኘሁት ነገር ተደላድዬ መቀመጥን አልፈልግም፡፡ አፍሪካ በሰዎቿ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አካሂዳለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ከተቋሞቻችን ብዙ ነገር ማግኘት እንደምንችል የምናስብ ሰዎች ተመልሰን በመምጣት፣ አፍሪካ ያላትን ነገር ማስፋፋት እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ አፍሪካ የልማት አጀንዳዎቿን ሊያጤኑ የሚችሉ የራሷን ባለድሎችና የራሷን ተቋማት የገነባች አኅጉር ናት፡፡ በርካታ አቅም ያላቸው አፍሪካውያን ስላሉም በጋራ ሆነን ማራኪ አኅጉር መገንባት እንችላለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ በየአገሩ ያሉትን ሀብቶች በማጎልበት መሥራቱ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ በእኔ ሥር ያሉት ሰዎች የፓን አፍሪካዊነት ስሜት ያላቸውና በበርካታ አገሮች ውስጥ ለብዙ ጊዜ የኖሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ውስጥ የሚቀጣጠል ጥልቅ የሆነ ስሜት አለ፡፡ ሁላችንም የጋራ አመለካከት አለን፡፡ አንዳችን ስለሌላችን የሚያገባን፣ ስለሌላችን የሚገደን ነን፡፡ አንዳችን ስለሌሎች አገሮች ባለቤትነት ይሰማናል፡፡ ይኼ ነው በዓለም ምርጡን ተቋም የመመሥረት ዓላማው፡፡ ሰዎች ከልባቸው ነገሩን ተቀበውለውት ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም በየአገሩ ልማትን ለማምጣት ይጠቀሙበታል ማለት ነው፡፡ በብሩንዲ ራሴን እንደ እንግዳ ወይም እንደ ውጭ ሰው አልመለከትም፡፡ በኬንያ ወይም በዚምባቡዌ እንግዳነት አይሰማኝም፡፡ በተለያዩ አገሮች ለበርካታ ዓመታት ኖሬያለሁ፡፡ የብዙዎቹን የልማት ተነሳሽነት ከልቤ እቀበለዋለሁ፡፡ ከትውልድ አገሬ ባሻገር ላሉት አገሮች የባለቤትነት ስሜት ይሰማኛል፡፡ ማንም ሰው እኔን በጠባብ አፍሪካዊነት ሊወነጅለኝ አይችልም፡፡ የበርካታ አገሮችን ባህልና አኗኗር እረዳለሁ፡፡ እንደ አገሬም እቆጥራቸዋለሁ፡፡ ባይተዋር አይደለሁም፡፡ ጋዜጠኛ ቢጠይቀኝ ምንም ሳልደናቀፍ ስለምጠየቀው የአፍሪካ አገር መናገር እችላለሁ፡፡ ስለዚህም ነው ባለድርሻዎቼ በእኔ ላይ እምነት የሚኖራቸው፡፡ ሰዎችን እኔን ለማመንና ከእኔ ጋር ለመሥራት የማይቸገሩት እውነተኛ አፍሪካዊ ልብ ስላለኝና በየትኛውም አገር ውስጥ ለመሥራት ከልብ የመነጨ ተነሳሽነት ስላለኝ ነው፡፡ ራሴን የምመለከተው እንደ ሉላዊ (ዩኒቨርሳሊስት) ሰው ነው፡፡
SOURCE, REPORTER
No comments:
Post a Comment