Wednesday, September 18, 2013

ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ መንግሥት የሕግ ጥበቃ እንዲያደርግ ዛሬም አጥብቀን እንጠይቃለን!! – ከ33ቱ ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ

 
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሠላማዊ ትግላቸውን አድማስ ለማስፋት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታና መተጠናከረ መንገድ በመላ ኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴያቸው ግን ከመንግሥት የሕግ ጥበቃ ከማጣቱ የተነሳ ፓርቲዎቹ ከፍ ያለ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ይህንን ሕገ-ወጥነት ሕዝቡ እንዲያውቀውና እንዲታገለው ይህንን መግለጫ ማውጣት አለስፈላጊ ሆኗል፡፡
ፓርቲዎቹ የተንቀሳቀሱባቸው ተግባራት በሕግ የተፈቀደላቸው ናቸው፡፡ አባላትን፣ ደጋፊዎችንና ሌሎችንም ዜጎች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ማወያየትና ከሕዝብ ጥቅም አንፃር ፓርቲዎች የሚደግፉትን ወይም የሚቃወሙትን አቋም ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ ሠላማዊ ሠልፍ መጥራት ከተግባራቶቻቸው አንዱ ነው፡፡ ሕዝቡን ወደ አዳራሽም ሆነ ወደ አደባባይ ስብሰባ ለመጥራትና ሠላማዊ ሠልፍም ለማደራጀት ደግሞ ፓርቲዎች በሕግ የሚጠበቅባቸው ከመንግሥታዊ አካላት ፈቃድ መጠየቅ ሳይሆን በሕግ መሠረት ማሳወቅ ነው፡፡ ስለ እንቅስቃሴያቸው ሕዝቡ እንዲያውቅላቸው ደግሞ በራሪ ወረቀቶችን ማሰራጨት፣ ፖስተሮችን መለጠፍ፣ በተሽከርካሪ ወይም በእግር እየተንቀሳቀሱ በድምጽ መቀስቀስ፣ በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ማስታወቂያ ማስነገርም ከፓርቲዎቹ የሚጠበቁ በሕግ የተደገፉ ተግባራት ናቸው፡፡ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2ዐዐዐ ዓም በግልጽ ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡
ከዚህ አንፃር የፓርቲዎቹን እንቅስቃሴና ከመንግሥት አካላት የደረሰባቸውን አፈናና ማሰቃየት መጥቀሱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በወላይታ፣ በአርባ ምንጭ፣ በፍቼና፣ በጎባ ከተሞች በተንቀሳቀሰባቸው ወቅቶች አባሎቻቸው ተደብድብዋል፡፡ ታስረዋል፡፡ የሥራ መሣሪያዎቻቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ለመኝታ ገንዘብ የከፈሉበት ሆቴል በር እንዲዘጋባቸውና ደጅ እንዲያድሩ ተደርገዋል፡፡ የ33ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ነሐሴ 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በአዲስ አበባ የመኢአድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ላዘጋጀነው ሕዝባዊ ስብሰባ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ወጣቶች በልደታ፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶና በአራዳ (ጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ) ታስረዋል፡፡ ለቅስቀሳ አገልግሎት የተከራየናቸው መኪናና የድምጽ ማጉያ መሣሪያዎችና በራሪ ወረቀቶች ለቀናት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ቆይተዋል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 26 ቀን በመስቀል አደባባይ ከጠራው ሠልፍ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ኃይሎች በፓርቲውና በአባላቱ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት መፈፀማቸውን የፓርቲው አመራሮች ገልፀዋል፡፡ የፓርቲው አባላት መታሰራቸውና መደብደባቸውንም አስረድተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የተፈፀመው በተቃዋሚ ፓርቲነት ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ሕግ በተፈቀደበት ሀገር ነው፡፡
በመንግሥት ኃይሎች በተወሰደው ርምጃ የተነሳ ፓርቲዎችና አባላት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በእቅዳቸው መሠረት እንዳይሰሩ መሰናክል ተፈጥሮባቸዋል፡፡ ለቅስቀሳ ዓላማ ለተገዙ ቁሳቁሶችና ለተከራዩ መኪኖችና ለሌሎች ወጭዎች የወጣው ገንዘብ ለኪሳራ እንዲዳረግ ተዳርገዋል፡፡ የታሰሩና የተደበደቡ አባላት አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ ጉዳት የደረሰው ከመንግሥት የሕግ ጥበቃ ባለመኖሩና ይልቁንም በመንግሥት ኃይሎች ሕገ ወጥ እርምጃ ምክንያት ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየው የዜጎች ሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣሱና በዚህም የሕግ ጥበቃ መጥፋቱ መረጋገጡን ነው፡፡ ከመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነቶች አንዱ የዜጎች መብቶች የሕግ ጥበቃ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ሆኖ ሳለ በተቃራኒው ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥታዊ አካል ዜጎችንና በሕግ መሠረት የተደራጁ ፓርቲዎችን በሕገ ወጥ እርምጃ ለማንበረከክ ሲንቀሳቀስ ይህ ለሐገር የከፋ ጉዳት አለው፡፡ ዜጎች በሕግ የበላይነት እምነት እንዲያጡ እየተደረገ ባለበት ሀገር ልማትን ሠላማምንና ዴሞክራሲን እውለ ለማድረግ የሚቻል አይደለም፡፡
በመሆኑም ስብስባችን በመንግሥት ኃይሎች በሕግ መሠረት በተቋቋሙ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎችን ለማፈንና ለማዳፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በጽኑ እያወገዝን፣
1. መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ከሚጥሱ ድርጊቶቹ እንዲታቀብና ለፓርቲዎች እንቅስቃሴ የሕግ ጥበቃ በማድረግ በተሻለ ሁኔታ በር እንዲከፍት፡፡
2. ሕዝብ ለሕግ የበላይነት መከበር የሚያደርገውን ትግል በባለቤትነት አጠንክሮ እንዲቀጥል፡፡
3. የዴሞክራሲ ኃይሎች ለሕገ መንግሥቱ ተግባራዊነት የተባበረ ትግላቸውን በይበልጥ እንዲገፉበት፡፡
4. የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለሕግ የበላይነት ከሚያደርገው ትግል ጎን እንድትቆሙ፡፡
5. የመገናኛ ብዙሃን በመንግሥት የሚፈፀሙ ሕገ መንግሥቱን የጣሱ እምርጃዎችን በተጨባጭ ለሕዝብ በማሳወቅ የሕዝብ ወገንተኛነታችሁን እንድታረጋግጡ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
መስከረም 7 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ
 
SOURCE, ABUGIDA

No comments:

Post a Comment