Monday, September 16, 2013

የመስከረም 12 ሰልፍ በታቀደለት ጊዜ ይካሔዳል (ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ማገለጫ), September 16, 2013

የመስከረም 12 ሰልፍ በታቀደለት ጊዜ ይካሔዳል!!!!!

ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ሊያካሂደው የነበረው የተቃዉሞ ሰላማዊ ሰልፍ በመንግስት ታጣቂዎች ህገ ወጥ እርምጃ ከተደናቀፈ በኋላ ነሐሴ 3ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ፓርቲው መስከረም 12 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሣወቂያ ክፍል እንዲያውቀዉ አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎ የሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሣወቂያ ክፍል ጳጉሜ 1 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ የሰለፉን ዓላማ፣ የሰልፉ ተሳታፊዎች የሚጓዙበትን መስመርና የሰልፉ መዳረሻ ከግንባታ ስራና ከፀጥታ ጥበቃ ጋር ያለውን ችግር አስመልክቶ ማብራሪያ እንደሚያስፈልግ በጠየቀዉ መሠረት፡-
Blue Party Ethiopia
1ኛ. የሰልፉ ዓላማ፤
በህገ መንግሥቱ የተደነገጉት ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበር፣ዜጐች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብታቸው እንዲከበር፣ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 11፡3 በግልፅ የተደነገገው መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለው ድንጋጌ እንዲከበር፣ መንግሥት የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ የሚሉትን ጥያቄዎች በሰላማዊ ሠልፍ መንግሥትን ለመጠየቅ መሆኑን፤

2ኛ. የሰልፉ ተሳታፊዎች የሚጓዙበትን መስመር
መነሻው ከፓርቲው ጽ/ቤት ግንፍሌ አካባቢ ተነስቶ በአራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል በኩል በአሮጌው ቄራ በአምባሳደር ቴአትር አልፎ መስቀል አደባባይ ሲሆን፣ በዚህ መንገድ ላይ ምንም ዓይነት የግንባታ ሥራ የሌለበትና ሠልፉ የሚደረገውም እሁድ ከጥዋቱ 3፡ዐዐ-7፡00 ሰዓት ባለው የእረፍት ቀን በመሆኑ በዕለቱ ምንም ዓይነት የመንግሥት ሥራና የትራፊክ መጨናነቅ የሌለበትና መድረሻ ቦታችንም መስቀል አደባባይ ከቅርብ ቀናት በፊት በኃይማኖት ተቋማት አስተባባሪነት ሠልፍ የተደረገበት መሆኑና ወደፊትም መስከረም 12 ቀን ከሚደረገው ሠልፍ አንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከሁሉም ማዕዘናት በሚመጡ ምዕመናን የመስቀል በዓል የሚከበርበት ቦታ መሆኑን ጳጉሜ 04 ቀን 2005 ዓ.ም በፃፍነው ደብዳቤ አብራርተናል፡፡

የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1987 አንቀፅ 6 ቁጥር 2 “የከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት በዚህ አዋጁ አንቀፅ 6 ንዑስ አንቀፅ 1 የተመለከቱትን በማገናዘብ ሰላማዊ ሰልፉ በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ስፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያት ካለው ምክንያቱን በመግለፅ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ12 ሰዓት ውስጥ በጽሑፍ ለአዘጋጁ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም የከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ምንጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሔድ አይችልም ማለት አይችልም” በሚለው መሰረት የእዉቅና ጥያቄ የቀረበለት አካል በፅሁፍ በ12 ሰዓት ውስጥ መልስ የመስጠት ግዴታ ቢኖርበትም እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
ፓርቲያችን በሕግ የሚጠበቅበትን ለሚመለከተዉ አካል የማሳወቅ ግዴታ በአግባቡ ስለተወጣና ለሰልፉም የሚያስፈልጉ ስራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም በታቀደው መሰረት ያካሂዳል፡፡ በመሆኑም በዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ የምናነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማሕበራትና ዜጎች በአጠቃላይ በሰልፉ ላይ በመሳተፍ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በመጨረሻም ሰላማዊ ሰልፉን በመቆጣጠርና የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ የሚያውክን ሁኔታ በማስወገድ የሰላማዊ ሰልፈኞች መብቶችን ለመጠበቅ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች በአዋጁ ቁጥር 3/1987 የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ተግባር በአግባቡ እንዲያከናውኑ እናሳስባለን፡፡
መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
SOURCE, ECADF

No comments:

Post a Comment