Monday, November 4, 2013

የአንድነት ፓርቲ የስራ አመራር አባል በወያኔ ቅጥረኞች ታግተዉ መደብደባቸዉ ተሰማ


የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በቅርቡ በመላዉ አገሪቱ ባካሄደዉ “የሚሊዮኖች ድምጽ” ዘመቻ ዉስጥ ከከተማ ወደ ከተማ በመዘዋወር ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉትና የፓርቲዉ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት መምህር አበበ አካሉ ባሳለፍነዉ ሳምንት ዉስጥ የደህንነት መስሪያ ቤት አባላት ነን ባሉ ሶስት ቅጥረኞች ታግተዉ ክፉኛ እንደተደበደቡና የግድያ ማስፈራሪያም እንደደረሰባቸዉ ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ዘገበ። አቶ አበበ አካሉ የደረሰባቸዉን ድብደባ አስመልክተዉ ለፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ እንደተናገሩት በምሳ ሰዓት ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ ለስራ ጉዳይ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወሩ ህገ ወጦቹ የወያኔ ደህንነት አባላት በላንድክሩዘር መኪና ተከትለዋቸዉ መንገድ ከዘጉባቸዉ አቶ አበበን በግድ መኪናወ ዉስጥ እንዲገቡ በማድረግ ወዳልታወቀ ቦታ ወስደዋቸዉ ደርቅ ሲሚንቶ ላይ አስተኝተዉ እንደደበደቧቸዉ ተናግረዋል።
ወንለኞቹ የወያኔ ቅጥረኞች መምህር አበበን ከቀኑ 6፡30 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ ሽጉጥ ደግነውባቸው የማያውቁትን የአልኮል ቃና ያለው ፈሻሽ ነገር በግድ በመጋት ከሲሚንቶ ጋር አጣብቀው በተደጋጋሚ የረገጧቸዉ ሲሆን በሰላማዊ መንገድ የሚያካሂዱትን ትግል እስካላቆሙ ድረስ መንግስትን በሀይል ለማውረድ እየሰራህ ነዉ በሚል የሽብርተኝነት ወንጀል እንደሚወነጅሏቸው ከነገሯቸዉ በኋላ እንደለቀቋቸዉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት መምህር አበበ አካሉ በአሁኑ ወቅት በመኖሪያ ቤታቸው ተኝተው በማገገም ላይ እንደሚገኙ ፍኖተ ነጻነት ጨምሮ ገልጿል።
SOURCE, GENBOT SEBAT WEBSITE

ወይዘሮ አዜብ መስፍን የፓርቲ መልቀቂያ አቀረቡ:



ወይዘሮ አዜብ መስፍን የፓርቲ መልቀቂያ አቀረቡ: ተቀባይነት አላገኘም::
ሕወሓት ለወይዘሮ አዜብ ስልጣን በመስጠት በስልት ልታጠምዳቸው ነው::

"ለእኔ ስም የሚያወጡልኝ ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ የሕወሓት ሹሞች ናቸው::" የሚሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት የሆኑት እና የሙስናዋ ወይዘሮ በመባል የሚታወቁት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ለፓርቲያቸው ያቀረቡት የፖለቲካ በቃኝ ማመልከቻ ተቀባይነት ማጣቱ ሲገለጽ የሕወሓት ከፍተኛ ሰዎች ወይዘሮ አዜብን ለማጥመድ በሚያስችል ስልጣን ላይ ሊያስቀምቷቸው እንዳሰቡ ምንጮቹ ጠቁመዋል::የደህንነት ሹሙ አቶ ጌታቸው በወይዘሮ አዜባ ጋር በዋዛ አንላቀቅም በማለት ቂም በቀላቸውን ሊወጡባቸው ይችላሉ የሚል ግምቶች በሕወሓት አከባቢ እየተነገሩ ነው::


ለወይዘሮ አዜብ የታሰበው ስልጣን የትኛው እንደሆነ ባይታወቅም በስልት ከፖለቲካ ለማፈግፈግ እና ለመልቀቅ ከአገር ለመውጣት እንደማይቻል ተነግሯቸዋል:: ወይዘሮ አዜብ በድጋሚ ማመልከቻ ማቅረባቸው እንደማይቀር የጠቆሙት ምንጮቹ ምንኛውም ስልጣን ቢሰጣቸው በአዲስ አበባ መስተዳደር ምክር ቤት ውስጥ አባል ሆነው የመቀጠል ፍላጎት እንዳሌላቸው በግልጽ ተናግረዋል::ባልቤቴ ከሞተ በኋላ በሕወሓት ተገፍቻለሁ የሚሉት ወይዘሮ አዜብ ምንም ነገር ሊመቻቸው እንዳልቻለ እና ስለ እሳቸው ውስጥ ለውስጥ የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች እያበሳጯቸው እንደሆነ ተናግረዋል በተጨማሪም ለእኔ ስም የሚያወጡልኝ ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ የሕወሓት ሹሞች ናቸው ሲሉ አማረዋል::

ምንሊክ ሳልሳዊ.

አርቲስት ደበበ እሸቱ ባለው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንየት ብሔራዊ ትያትር እንዳይገኝ እና ስሙ እንዳይጠራ ተወሰነበት











አርቲስት ማለት በተፈጥሮ ያገኘውን ጸጋ ተጠቅሞ መልእቱን ማስተላለፍ የሚችል በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በስነጽሁፍ፣ በቲያትር… ሊሆን ይችላል፡፡ አርቲስቶችም ይህን ጸጋ ተጠቅመው ሰዎችን በዙሪያቸው በማሰባሰብ ህልሞቻቸውን ወይም ያለውን ነባራዊ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳዮች እያነሱ ሰላምን አንድነትን ፍቅርን ይሰብካሉ፤ በስራዎቻቸው ሪፖርት ያደርጋሉ፤ ይተንትናሉ፤ ይቀሰቅሰቀሉ፤ አንዳንድ ድብቅና የታፈኑ ጉዳዮችን ያላቸውን ፀጋ ተጠቅመውም ያጋልጣሉ፤ ብቻ በአጠቃላይ አርቲስቶች ከማዝናናት በዘለለ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በሚፈጠር እድገት ትልቅ ሚና ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ምስቅልቅል ባለ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ በምትገኝ ሀገር ከሁሉ በተሻለ አርቲስቶች ህብረተሰቡን የማረጋጋትና የማቀራረብ እንዲሁም ውስጣዊ ሰላሙን እንዲያገኝ የማስቻል፤ ሀገሪቷንም ነባራዊ ሁኔታ የማሳየትና መፍትሄዎችን እስከመጠቆም ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ከማንም በከፋ እንደውም አርቲስቶቻችን ለማህበረሰቡ ማበርከት የሚገባቸውን አገልግሎት ትተው፤ ጭራሽ ለየትኛውም ወጣት እና ህጻናት አርአያ መሆን የማይችሉ ንዋይ አምላኪዎች ሆነው እነሱ ራሳቸው ችግር እየሆኑብን ተቸገርን፡፡
እንዲህ እንዳወራ ያደረገኝ ባለፈው ሳምንት ይድነቃቸው ከበደ “በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ – እውነትና ከሕደት…” ብሎ የጻፈውን እንዳነበብኩ በእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያለው የመንፈስ ክስረትና ክሽፈት ከስርአቱ ጋር የሚደረገውን ትግል ምን ያህል ከባድ እንዳረገው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በህይወት ካሉት አርቲስቶች ግንባር ቀደሙና አንጋፋው ስለመሆኑ ለመከራከር መሞከር ሞኝነት ነው፡፡ ጋሽ ደቤ የሰራቸውን ስራዎች መጨረሻ ላይ በከፊል ለማስቀመጥ እሞክራለሁ ግን፡፡ ግን ዛሬ “አርቲስት” ነን የሚሉ ሰዎች ይህንን አንጋፋ የሙያ አባታቸው እና መምህራቸው ፤ እነ ጋሽ ደበበ በስንት መስዋዕትነት የከፈቱላቸውን መንገድ ተጠቅመው ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ሲያበቋቸው ባያመስግኗቸው እንኳ ምናለ እውቅና እንኳ ባይነፍጓቸው፡፡ ጋሽ ደቤ ስንት ትያትሮችን ያዘጋጀበት የተወነበት በስራ አስኪያጅነት የመራበትእና ያስተማረበት ብሔራዊ ትያትር በህይወት ያሉ እና የሌሉ አንጋፋ አርቲስቶችን ለማመስገንና ለማወደስ ያዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ጋሽ ደቤን ባለው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንየት እንዳይገኝ እና ስሙ እንዳይጠራ በስምምነት መወሰናቸው፤ ከመካከላቸውም ይህንን ተቃውሞ አንድም አርቲስት ድምጹን ለማሰማት አለመሞከሩ ያለንበት ማህበራዊ ዝቅጠት ደረጃን ዘግናኝ አድርጎታል፡፡ ጋሽ ደቤ በግል ህይወቱ ለማንኛውም ወጣት አርአያ መሆን የሚችል ጠንካራ ቤተሰብ ያለው የተረጋጋ እና ለህሊኒው የሚገዛ ስለመሆኑ የኔ ዲስኩር ሳይሆን እየኖረ ያለው ህይወት ምስክር ነው፡፡ ጋሽ ደቤ እንደሌሎቹ አርቲስት ነን ባዮች ቢያጎበድድ ምናልባትም ሀገሪቷ ውስጥ ካሉ ሚሊየነሮች ተርታ ተሰላፊ እንደ ሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
በጅብ ሊቀመንበር በጦጣ ጸሀፊ
አንቺ ሰባ ሰባት ቶሎ ቶሎ እነፊ፤
ነበር ያለው የወሎ ሰው፤ ጋሽ ደቤ ለታሪክ የሚተላለፉ ህያው ስራዎች ሰርቷል እነዚህን ስራዎቹን በምንም ሊፍቋቸው እና ሊያጠፏቸው አይችሉም፡፡ የእውነት ዘመን ሲመጣ ለአደባባይ ይበቃሉ፡፡ አያድርገውና ጋሽ ደቤ የሆነ አደጋ ላይ ቢሆን እነዚህ የብሔራዊ ትያትር “አርቲስቶች” የጋዜጦችና መጽሔቶች የሽፋን ገጾችን እንዴት እንደሚያጨናንቁ አስቡት ዛሬ ግን የብሔራዊ ትያትር እንዳይጋበዝ ሲከለከል እንዳቸውም ድምጻቸን ለማሰማት አልደፈሩም፡፡ ነገር ግን ጋሽ ደቤ የእውነት ስራዎቹን የሚያደንቁለትና የእሱን አርአያ የሚከተሉ ወጣቶች አሉ፡፡
“አያናግረንም የያዘን አባዜ
ዝም አያሰኘንም የያዘን አባዜ
እንደው ፍዝዝዝዝ ያሰኘናልሳ
ቅጥ አምባሩ ያጣ የቁም ሞት አባሳ፡፡”
እስቲ ጋሽ ደቤ ከሰራቸው ስራዎች ውስጥ በጥቂቱ እንያቸው፤ በሃገር ውስጥ ካለው ታዋቂነትና ለሙያው ካደረገው አስተዋጽኦ ለመጠቀስ ያህል ፡-
በመድረክ ላይ
በቤተኪነጥበባት ወቴአትር
ያላቻ ጋብቻ ተዋናይ
ሮሚዎባ ዡልየት ተዋናይ
ጠልፎ በኪሴ ተዋናይም አዘጋጂም
ዳንዴው ጨቡዴ ››
ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ (በእንግሊዝኛ) ተዋናይ
ኦቴሎ (በአንግሊዝኛ) ተዋናይም አዘጋጂም
አዳ ኦክ አራክል (በእንግሊዝኛ)ከሎ.ጸ.ገ.መ ተዋናይ
በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ(ብሔራዊ) ቴአትር
የበጋ ሌሊት ራዕይ ተዋናይ
አንድ ዓመት ከአንድ ቀን ተዋናይ
እናት ዓለም ጠኑ ተዋናይ
ኪንግ ሊር ተዋናይ
ዋናው ተቆጣጣሪ ተዋናይ
ጠያቂ ተዋናይ አዘጋጅ
በቀይካባ ስውር ደባ አዘጋጅ
ተሓድሶ አዘጋጅ
የአዘውንቶች ክበብ አዘጋጅ ተዋናይ
በሃገር ፍቅር ቴአትር
ጠልፎ በኪሴ አዘጋጅ/ተዋናይ
የወፍ ጎጆ ተዋናይ
ኪንግ ሊር ተዋናይ
የቬኒሱ ነጋዴ ተዋናይ
ናትናኤል ጠቢቡ ተዋናይ
ድብልቅልቅ ተርጓሚ/ ተዋናይ
ማዕበል ተርጓሚ አዘጋጅ
በፊልም በሃገርና በዓለም አቀፍ
ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር
ሻፍት ኢን አፍሪካ
ጉማ
ዚ አፍሪካን ስፓይ
ዜልዳ
አፍሪካ
ዘግሬቭ ዲገር
ዘ ግሬት ሪቤሊየን
እነዚህ ለምሳሌ ያህል የቀረቡ እንጂ የደበበ ስራዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ከመድረክና ፊልም ስራዎቹ ባሻገር ተማሪዎችም አሰልጥኗል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በብሔራዊ ቴአትር የተዋንያን ስልጠና ማዕከል ሲያቋቁሙ ከመምሃራኖቹ መሃልና በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው መምህር ደበበ ሲሆን ለተማሪዎቹም መማርያ እንዲሆን የተረጎመው የስታንስላቭስኪ የተዋናይ ሀሁ ለበርካታዎች የሙያ ተማሪዎች የሙያቸው ፊደል መቁጠርያ ሆኖ ይገ ኛል፡፡
በትርጉም በኩልም ደበበ ከቴአትር
ያልታመመው በሽተኛ
ድብልቅልቅ
ጎርፉ
ከመጽሐፍ ደሞ
የዳዊት ወልደጊዮርጊስን
የደም እንባ
የራሱን ወጥ ሥራ በተመለከተ
የእምነቴ ፈተና
ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው
ደበበ ለአፍሪካ ጥበብ ያለውን አመለካከትና ግንዛቤ ከቅኝ ገዢዎች ትርጓሜ ለማውጣትና ሶስተኛው ዓለም ኋላ ቀር ሲባልም በኤኮኖሚና በቴክኒዮሎጂ እንደሆነ፤ ይህም የሆነው ነጩ የአፍሪካን የዋህነት፤ እንግዳ ተቀባይነትና ሩህሩህነት መንጠላጠያ በማድረግ ቅኝ አድርገው ህሊናውን ስለዘጉበትና ስላሰሩት መሆኑን፤በባህል በኩል ግን ጨርሶ ሊደርሱበት የማይችሉትና ሊያጠፉትም ያደረጉት ሙከራ ዋጋ ቢስ ሆኖ እንደቀረ የሚያስረዳ ጥናታዊ ጽሁፍ በማቅረብ ተቀባይነትን አግኝቶ ድል ያደረገና፤ ቀደም ሲል የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል በ1985 ዓ/ም እንደ አውሮፓውያን ቆጣጠር በርሊን ላይ በተካሄደው የዩኔስኮ የባህል(አይ ቲ አይ) ኢንተርናሽናል ቴአትር ኢትዮጵያን ወክሎ በመገኘት በአፍሪካ ውስጥ የመጀመርያው ፕሮፌሽናል ቴአትር ቤት የሃገር ፍቅር ቴአትር መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ በዚሁ ዓመት የዩኔስኮ የባሕል ክፍል አይ ቲ አይ የአፍሪካ ተጠሪ ሆኖ በመመረጥ፤ በዚያው ዘመን ዝምባብዌ ላይ በሚካሄደው ቴአትር ለልማትና ዕድገት ወርክሾፕ ላይ በመሪነት እንዲገኝ በዩኔስኮ ተወክሎ በመሄድ ወርክሾፑን በአጥጋቢ ችሎታውና የአመራር ብቃቱ ከመፈጸሙም ባሻገር ለብዙ ጊዜ ተሞክሮ ሲወድቅ ሲነሳ የነበረውን የአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ማሕበርን አስተባብሮ በማቋቋም የማሕበሩም መስራች ፕሬዜዳንት ሆኖ ለ12 ዓመታት መርቷል፡፡ አሁንም መስራች ፕሬዛዳንት በመባል ይጠራል፡
ደበበ በችሎታውና በብቃቱ በማስተባበር ችሎታው ዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያን ለማዘጋጀት ሲወስን ደበበንም አፍሪካን በመወከል የኤዲቶርያል ቦርድ አባል አድርጎ መድቦት ሥራውን በሚገባ ተወጥቷል፡፡
ደበበ ቴአትር ለልማትና ለእድገት በሚል የሚታወቀውን የቴአትር ዲሲፕሊን ስልጠና ለበርካታ ሃገራት ባለሙያዎች ያስተማረ ሲሆን በርካታ ወርክሾፖችም በየሃገራቱ እየተጋበዘ መርቷል፡፡ ይሀን ዘዴ ካዋቀሩትም አምስት አፍሪካዊ ባለሙያዎች አንዱ ደበበ ነው፡፡
ወርክሾፕ የሰጠባቸው ቦታዎች፤
ታንዛኒያ፤ኡጋንዳ፤ኬንያ፤ማላዊ፤ኮንጎ ብራዛቪል፤አይቮሪ ኮስት፤ ካሜሩን፤ ናይጄርያ፤አይርላንድ፤ብራዚል፤ሰሜን አሜሪካ፤እንግሊዝ፤ ኩባ፤ በርሊን፤ካናዳ ይገኙበታል፡፡
ደበበ ላለፉት ከ40 በላይ ዓመታት በቴአትር ጥበብ ውስጥ ኖሮ በ1995 በተካሄደው ሃገራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ‹‹ቀስተደመና›› የፖለቲካ ፓርቲን ተቀላቅሎ፤ በኋላም ቅንጅት ሲፈጠር የምክር ቤት አባልና የሕዝብ ግንኙነት በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ቅንጅትን ለድል ያበቃ፤ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ዝግጅቶቹ ገዢውን ፓርቲ ያንበረከኩና ቅንጅትና ያገዘፉ ነበሩ፡፡በዚህም ከሌሎች አመራሮች ጋር ለአንድ ዓመት ከአስር ወራት ለእስር ተዳርጓል፡፡ እንዲሁም በ2002 በድጋሚ ለአንድ አመት ታስሮ ተፈቷል፡፡
በሱ ሙያ የተሰለፉ ‹‹አይተነው ጊዜ›› ሲሉ እሱ ግን ‹‹እኔም ድርሻ አለኝ›› በማለት ቤተሰቡን፤ ምቾቱን፤ ተድላውን፤ ሁሉ ችላ በማለት ክግል ይልቅ ለህብረተሰቡ፤ ከራሱ ይልቅ ለወገኑ በመወገን የተሰለፈ ብቸኛ የጥበብ ሰው ነው፡፡አንዳንዶች ሹመትና ገንዘብ ሲያታልላቸው፤ እሱን ያታለለው ግን ነጻነት ፍትህና ዴሞክራሲ ከሰብአዊ መበት መከበር ጋር ነው፡፡ለዚህም ነው ከማንም በላይ ሕዝባዊ የክብር ዘውድ የተደፋለት፡፡ ዛሬ ያንን ዘውድ ደፍቶ ባናየውም ታሪክ ግን እንዳለበሰው ይኖራል አንድ ቀን ይሀም ይፋ ሆኖ ይከበራል፡፡
ደበበ በሃገሩ ለመሸለም ባይበቃም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ለሽልማቶች የበቃ ባለሙያ ነው፡፡ለዚሁ የሙያ አስተዋጽኦ ክፍተኛው ክብሩ በአትላንታ ጆርጂያ ኖቬምበር 24 የደበበ እሸቱ ቀን ተብሎ እንዲሰየም የከተማው ምክር ቤት ማጽደቁ ነው፡፡
ጋሽ ደቤ ጋደኛም ሚስትም ከሆነችው ከአልማዝ ደጀኔ ጋር 4 ልጆች እና 6 የልጅ ልጆች ያሉት ሲሆን ሰኔ 2005 ዓ.ም 40ኛ ዓመታቸውን ከልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው በተገኙበት አክብረዋል፡፡
ፍቅር ሰላም እና ጤና ለጋሽ ደቤ አብዝቶ ይስጥልን!
(የጋሽ ደቤን ስራዎች በተመለከተ ወንድወሰን አንድአርጋቸው 2001 ዓ/ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመመረቂያ ካዘጋጀው ሥራ እንዲሁም “የእምነቴ ፈተና “ ከሚለው የጋሽ ደቤ መጽሐፍ መግቢያ ላይ አለምፀሀይ ወዳጆ ከጻፈችው ምስክርነት የተገኘ ነው)

Sunday, November 3, 2013

አሳዛኝ ዜና- ስደተኞቹ በሙሉ አለቁ!




ከኒጀር ተነስተው ፣ ሰሃራ በረሃን በማቋረጥ አልጄሪያ ለመድረስ፣ ከዚያም ወደ ሌላ አገር ለመሻገር አንድ መቶ የሚሆኑ ስደተኞች በአንድ መኪና ታጭቀው ጉዞ ይጀምራሉ።
ሰሃራ በረሃን እንዳጋመሱ የተጫኑበት መኪና ይበላሻል። በዚያ በረሃ፣ መኪና ጠጋኝ ቀርቶ ፣ ቀና ቢሉ ሰማይ፣ ጎንበስ ቢሉ ድንጋይ ካልሆነ ምንም አልነበረም። የሚያደርጉት ጠፋቸው። ማንም የሚደርስላቸውም አልነበረም። በዚህ ሁኔታ ቀናት ተቶጠሩ። የቋጠሯት ጭብጦና እፍኝ ውሃ አለቀች። ቀስ በቀስም አንድ በአንድ እያሉ በውሃ ጥምና በረሃብ ይሞቱ ጀመር።
በመጨረሻም አንድ ዘላን ድንገት ሲያልፍ ያየውን በመናገሩ በሂሊኮፕተር ከስፍራው ሲደረስ ሁሉም፣ አንድም ሳይቀር፣ በውሃ ጥም ሞተውና ወድቀው፣ አንዳንዶቹም ባልታወቀ አውሬ ተበልተው ተገኙ። የበለጠ የሚያሳዝነው 92ቱ ሴቶችና ህጻናት ናቸው። ዜናውን ሲ ኤን ኤን ዛሬ ኦክቶበር 31 አወራው -

“ከ6 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባል አንዱ ብሆን ምን ችግር አለው?” አቶ ልደቱ አያሌው “ከ6 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባል አንዱ ብሆን ምን ችግር አለው;

” “ወ/ት ብርቱካን የተሰጣት ኃላፊነት 

አግባብ አይደለም” “እንባ አውጥቼ 

አልቅሼ ኃላፊነት በቃኝ እያልኩ ነው 

የተመረጥኩት” “ከኢንጂነር ኃይሉ 

እንዲሕ ያለ ውሸት አልጠብቅም ነበር”

“የእስክንድር ነጋ ጋዜጣ ቅንጅትን ወደተሳሳተ አቅጣጫ 

ገፍቷል”

- አቶ ልደቱ አያሌው

lidetu
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው መውጣት የጀመሩት በ1990ዎቹ ሲሆን፣ ከምርጫ 97 ዋዜማ አንስቶ አነጋጋሪነታቸው በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ከሁለት ዓመት የእንግሊዝ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱት አቶ ልደቱ አያሌው ጋ፣ የሎሚ መፅሔት አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡-
ሎሚ፡- ለረዥም ጊዜያት ከሚዲያም ከፖለቲካም ርቀኻል፤ በሠላም ነው?
ልደቱ፡- እንደሚታወቀው ሀገር ውስጥ አልነበርኩም፡፡ በኢዴፓ ውስጥ የነበረኝን የሥራ አስፈፃሚ ኃላፊነትም አስረክቤ ስለነበር ወደ ሚዲያ የምመጣበት ዕድል አልነበረም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፖለቲካችን ወደተስተካከለ መስመር ለመግባት ስለተቸገረ፤ አንዳንድ ጊዜ ለሀገር፣ ለሕዝብ ይጠቅማል ብለህ የምትሰራውና የምትናገረው ነገር በሌሎች ዘንድ ትርጉሙ እየተለየ ሲያስቸግር፣ ሰዎች በነገሮች ላይ የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኙ ፋታ መስጠትም ይጠቅማል ብዬ ነው፡፡ እንጂ ሌላ ምክንያት ኖሮኝ አይደለም፡፡
ሎሚ፡- ከፓርላማ የአምስት ዓመት ቆይታህ በኋላ የነበረው ጊዜህን በምን ነበር ያሳለፍከው?
ልደቱ፡- ፓርላማ አምስት አመት ነው የቆየሁት፡፡ የፓርላማው አሠራር በሚፈቅደው መሠረት እንደ ፓርቲያችንን ወክለን ተሣትፎ ስናደርግ ነበር፡፡ በተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥም የተወከሉ ነበሩ፡፡ ከኛ ፓርቲ አቅማችንና ሁኔታው በፈቀደው መጠን ለነዛ ኮሚቴዎች ገንቢ የሆነ ተሣትፎ ለማድረግ ጥረት አድርገናል፡፡ እኔም እንደ ሕዝብ ተወካይነቴ ክርክሮችና ውይይቶች ሲኖሩ የራሴን ዝግጅት አድርጌ ከፓርቲያችን አቋም አንፃር ሃሣቡ ተቀባይነት ያግኝም አያግኝም የሚታየኝን፣ የሚመስለኝን አቋም በማራመድ በጐ ተሣትፎ አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሞላ ጐደል ጠቃሚ ተሣትፎ ነበረን ብዬ አምናለሁ፡፡ እኛ ፓርላማ ብንገባም ባንገባም፣ የተቃዋሚው ጎራ በአብዛኛው ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከፓርላማ መውጣቱ ያሳዝነኛል፡፡ ይህ ሂደት ተጠናክሮና ጐልብቶ ፓርላማችን የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚንፀባረቁበት መድረክ ሆኖ የሚቀጥል መስሎኝ ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ ወደኋላ ነው የሄድነው፡፡
ሎሚ፡- በርካታዎች በምርጫ 97 ሠሞን ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብለው ይገምቱ ነበር፤ አንተስ?
ልደቱ፡- Well እንግዲህ፡፡ በ1997 ዓ.ም. ለውጥ ለማምጣት አንድ ዕድል ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ግን መጀመሪያ ለውጥ ማለት ምንድነው? በሚለው መስማማት አለብን፡፡ ምናልባት ለውጥ ለማምጣት 97 ላይ ዕድል ነበር ሲባል አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት መንግስታዊ ለውጥ ማምጣት ከሆነ የተለየ ነው፡፡ እኔ በዚህ በኩል ብዙ ዕድል ነበር ብዬ አላምንም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ገንቢ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ከሆነ እስማማለሁ፡፡ ሰዎች ለውጥን የሚያዩበት መንገድ ይለያያል፡፡
ለእኔ 1997 ዓ.ም. የመንግስት ለውጥ የሚመጣበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ያን ደግሞ የምናውቀው ምርጫ ውስጥ ከገባን በኋላ ሳይሆን ወደ ምርጫ ለመግባት ዝግጅት ስናደርግ ነው፡፡ ይህንንም በኢዴፓ ደረጃ ተወያይተንበት፣ ነባራዊ ሁኔታውን ገምግመን የያዝነው ጉዳይ ነበር፡፡ “…በዚህ ምርጫ አሸንፈን አዲስ አበባ ከተማን እንቆጣጠራለን፤ በቂ የሚባል የፓርላማ መቀመጫ  እንይዛለን፤ ይሄን ውጤት ይዘን ከአምስት አመት በኋላ በሚደረግ ምርጫ ደግሞ መንግስት ለመሆን የሚያስችለንን ዕድሉን እናገኛለን” ብለን ነው ተሳትፎ ያደረግነው፡፡
በምርጫ ስትሣተፍ “አሸንፋለሁ” እያልክ ነው መቀስቀስ ያለብህ፡፡ ይህ የግድ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ግን በውስጣችን ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በ97 መንግስት ለመለወጥ የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም፡፡ አንድ ቀላል ምሣሌ ላንሳ፤ ቅንጅት በዚያ ምርጫ ከባድ ተፎካካሪ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ ግን በ130 ወረዳዎች ተፎካካሪ አላቀረብንም፡፡ ይሄ በራሱ ሙሉ ለሙሉ እንዳናሸንፍ ያደረገ አንድ ችግር ነበር፡፡
lidetu-ayalew-and-muse-semuበወቅቱ እኛ ብቻ አልነበርንም በተቃዋሚነት ምርጫ ፉክክር ውስጥ የገባነው፡፡ “ህብረት” ውድድር ውስጥ ነበር፤ እኛና ህብረቱ የምንካፈለው የሕዝብ ድምፅ ነበር፡፡ ሁለታችን ለየብቻ ስለተወዳደርን የተቃዋሚውን ድጋፍ ለሁለት እንካፈለዋለን፡፡ ይህ ደግሞ ኢህአዴግ በብዙ ቦታዎች ላይ በአነስተኛ ድምፅ የሚያሸንፍባቸውን ሁኔታዎች ፈጥሮ ነበር፡፡ ሌላው እንደተቃዋሚ ብዙ ያልሰራንባቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ቅንጅቱን እንደ ነፍጠኛ እና እንደ አማራ ኃይል የሚያይና በኢህአዴግ ተጠቃሚ ነኝ የሚል ክፍል ነበር፡፡ እነዚያ የሕብረተሰብ ክፍሎች እኛን እንደማይመርጡ ግልፅ ነበር፡፡
ምርጫው ግልፅና ፍትሃዊ እንደማይሆንም ቀድመን እናውቅ ነበር፡፡ ለምሣሌ ወደ 905 ሺህ ሰው በታዛቢነት ማቅረብ ነበረብን፡፡ እኛ ያቀረብነው 15 ሺህ ታዛቢ ነው፡፡ ይህ የሚያሣየው ወደ 85 ሺህ ታዛቢ ልናቀርብበት የምንችልበት ቦታ ክፍት መሆኑን ነው፡፡ በኒዚያ ቦታዎች የማጭበርበሩን ሁኔታ ማስቀረት ይቅርና ታዛቢ ባቀረብንባቸው ቦታዎች እንኳን ምርጫው ስለመጭበርበሩና አለመጭበርበሩ መረጃ ልናቀርብ የምንችልበት ዕድል አልነበረም፡፡ ታዛቢ አጥተን ያላቀረብንበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ከነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች አንፃር በ97 ምርጫ ለውጥ ለማምጣት ዕድል አልነበረም፡፡
ሎሚ፡- አሁን ከዘረዘርካቸው ምክንያቶች በተጨማሪ በምርጫ 97 የተቃዋሚዎችን ዕድል ያጨናገፈው አቶ ልደቱ አያሌው መሆኑ ይነገራል፤ አሁን ላይ ሆነህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
ልደቱ፡- ይባላል! በነገራችን ላይ ለዚህ ጥያቄ ብዙ ጊዜ መልስ ሰጥቻለሁ፡፡ መሠረት የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ አሉባልታ ነው፡፡ ተጨባጭ ነገር አይደለም፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ደጋግሞ ይመጣብሀል፡፡ እኔ ስለ አሉባልታ ማውራት ትቻለሁ ብቻ ሳይሆን ተጠይፌያለሁ፤ አንገፍግፎኛል፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ወይም አንዳንድ ድርጅቶች በሃሣብ ደረጃ ስትሞግታቸው መልስ የሚሰጡህ በሀሣብ አይደለም፡፡ በአሉባልታ ነው፡፡ ስለዚህ ያን ለማስተባበል አንተም አሉባልታ ማፍራት ትጀምራለህ፡፡ ሁሉም ይቆሽሽና ፖለቲካው አስቀያሚ ይሆናል፡፡
ጥያቄውን ለመመለስ ያነሳኸው ጉዳይ ሲባል እሰማለሁ፤ ቅንጅትን ልደቱ አፈረሰው ይባላል፡፡ እንደዚህ የሚሉ ሰዎች አንዳች ተጨባጭ መረጃ የላቸውም፡፡ እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ፡፡ ቅንጅት የአራት ፓርቲዎች ውህደት ወይም ጥምረት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ቅንጅትን ባሻው ጊዜ፣ በራሱ ፍላጐትና እምነት ተነስቶ የሚያፈርስ ከሆነ ምን ዓይነት ቅንጅት ነበር?… የአራት ድርጅቶች ሕብረት አልነበረም ማለት ነው፡፡ እኔ ስፈልግ የማፈርሰው ከሆነ ደግሞ ራሴ ብቻዬን ቅንጅት ነበርኩ ማለት ነው፡፡
ሰዎች ለቅንጅት ያላቸው አመለካከት የተለየ ነበር፡፡ በጣም ጠንካራና ግዙፍ አካል አድርገው ነበር የሳሉት፡፡ በሌላ በኩል ያን አግዝፈው የሳሉትን ቅንጅት “ልደቱ” የሚባል አንድ ግለሰብ አፈረሰው ይላሉ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ አይደለም ልደቱ፣ ኢዴፓ የሚባል ፓርቲ ቅንጅትን ሊያፈርሰው አይችልም፡፡ ምክንያቱም የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ነውና፡፡ ከአራቱ ፓርቲዎች አንዱ ፓርቲ ፍላጐት ሣይኖረው ቢወጣ ሦስቱ ፓርቲዎች ቅንጅት ሆነው መቀጠል ስለሚችሉ ሊያፈርሰው የሚችል ምክንያት የለም፡፡ አንድም ቀን “ቅንጅት የኛ ቅንጅት ሆኖ አይቀጥልም” ብለን ክስ አቅርበን አናውቅም፡፡ መስማማት ከቻልን በጋራ መቀጠል እንችላለን፤ ካልቻልን ግን እኛን ተዉንና እናንተ ቀጥሉ ነው ያልነው፡፡
ሦስቱ ድርጅቶች ቅንጅት ሆነው መቀጠል ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ አሉባልታው ምንም መሠረት የለውም፡፡ አንዳንድ ሰው ልደቱ ያፈረሰው ሊመስለው ይችላል፡፡ በሆነ አጋጣሚ የተወሩትን አሉባልታዎች መሠረት አድርጐ ወይም ከቅንጅት አገኘዋለሁ ብሎ የነበረውን አጉል ተስፋ ሲያጣ ጥፋቱን የሆነ አካል ላይ ወርውሮ በእከሌ ጥፋት ነው ቅንጅት የፈረሰው ሊል ይችላል፡፡ አልፈርድም! ሰው ብዙ ተስፋ አድርጐ ነበር፡፡ ያንን ተስፋ ሲያጣ፣ ተስፋ የጣለበትን ምክንያት የሆነ አካል ላይ መወርወር ነበረበት፡፡ ስለዚህ እኔ ላይ ወረወረው፡፡ ችግሩን ልረዳ እችላለሁ፡፡
ቅንጅትን በማፍረስ ረገድ ሚና ካለኝ እኔ ከቅንጅት ተለየሁ አይደል?… የቅንጅት አመራሮች እስር ቤት ገቡ፤ ከሁለት አመት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ወጥተው አንድ ላይ መስራት ጀመሩ፡፡ ችግሩ እኔ ከሆንኩ እኔ በሌለሁበት ቅንጅት ጠንካራ ሆኖ መቀጠል ነበረበት፡፡ ግን ቀጠለ?… የቅንጅት አመራሮች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ አብረው መስራት ቢጀምሩም ወደ ስምንትና ዘጠኝ ቦታ ከመከፋፈል አልዳኑም፡፡ ስለዚህ ቅንጅትን ያፈረሰው ልደቱ አልነበረም፤ የማፍረስ አቅምም አልነበረውም፡፡ ቅንጅት የፈረሰው በራሱ ውስጣዊ ድክመት ነው፡፡ እኛ ፓርላማ እንግባ ነው ያልነው፡፡ አዲስ አበባን ያኔ ተቀብለን ይዘን ቢሆን ኖሮ አሁን ያለው የትግል ሁኔታ በጣም የተለየ ይሆን ነበር፡፡
ሎሚ፡- በወቅቱ የያዛችሁት አቋም “እውነተኛውን ዴሞክራሲ መፍጠር” የሚል ነበር፤ በዚህ መንገድ እየተጓዛችሁ ሳለ አንተ ግን ቅንጅት ሲዋሃድ የሥልጣን ጥያቄ ማቅረብሕና በኋላም ማኩፈፍህ ነበር የተነገረው፤ ይህ ለምን ሆነ;
ልደቱ፡- ልደቱ “ስልጣን ይገባኛል ብሎ ነበር” ብሎ በመረጃ አስደግፎ የሚመጣ ሰው ካለ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ኃላፊነት መውሰድ እችላለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብተህ የስልጣን ጥያቄ ማቅረብ ስህተትም ወንጀልም አይደለም፡፡ ፖለቲካ የስልጣን ጥያቄ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ በኢዴፓ/መድህን ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ሰባት አመታት ሳልፈልግ ተመርጬ ነው አመራር የሆንኩት፡፡ ሳልፈለግ ስልህ አልፈልግም ብቻ ሣይሆን በአንደኛው ጉባኤ እንባ አውጥቼ አልቅሼ ኃላፊነት በቃኝ እያልኩ ነው የተመረጥኩት፡፡
በኋላ በነበሩት ሂደቶች ኢዴፓ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ፣ ችግር ላይ ስለነበር የአመራርነቱን ሚና ትቼ መሄድ አልፈለግኩም፡፡ ፈልጌም ነው የተመረጥኩት፡፡ በተለይ ደግሞ የቅንጅት አመራር ሆኜ ስመረጥ የመመረጥ ፍላጐት አልነበረኝም፡፡ እንባ አውጥቼ መድረክ ላይ ወጥቼ ለምኛለሁ፡፡ እምቢ ተብዬ ነው የሆንኩት፡፡ ቅንጅት ውስጥ እያለሁ ከኃላፊነቴ ለመልቀቅ ሦስት ጊዜ መልቀቂያ አቅርቤያለሁ፡፡ የኃላፊነት ፉክክር ውስጥ አንድም ቀን ገብቼ አላውቅም፡፡
ሎሚ፡- ኢንጂነር ኃይሉ ከሥልጣን ወርደው አንተ ለመሾም ጥያቄ አላቀረብክም?
ሰሞኑን ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ያወጡት መፅሐፍ ላይ “ልደቱ እጁን አውጥቶ ኢ/ር ኃይሉ ሻውልን ከስልጣን አውርዳችሁ እኔን ሊቀመንበር አድርጉኝ” ብሏል ብለው መፃፋቸውን ሰምቻለሁ፡፡ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ በቅንጅት ውስጥ ብዙ ሰዎች ነው የነበሩት፡፡ ኢ/ር ኃይሉ ያሉት “እውነት ነው ውሸት ነው” ማመዛዘን የሚችልና ህሊና ያለው ሰው ሊፈርድ ይችላል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ መድረክ ላይ እጁን አውጥቶ እከሌን አውርዱትና እኔን ሹሙኝ ብሎ አይጠይቅም፡፡ በፍፁም እንደዚህ ዓይነት ነገር አድርጌ አላውቅም፡፡ ተመኝቼውም አላውቅም፡፡ ቅንጅት ውስጥ በነበረው ሂደት ያለመመረጥ፣ ስልጣን ያለመያዝ ፍላጐት ነው የነበረኝ፡፡
ምናልባት ፕ/ር መስፍን በጋዜጣ ፅፈውት አንብበህ ሊሆን ይችላል፤ “ልደቱ ሁልጊዜ መመረጥ የሚፈልገው ቤቱ ቁጭ ብሎ ነው፤ ሎቢ ማድረግ አይፈልግም” ብለው ነው የተናገሩት፡፡ እኔ በትግሉ ውስጥ ተሣትፎ ማድረግና የሚገባኝን ስራ መስራት ነው የምፈልገው እንጂ ስልጣን መያዝ አይደለም፡፡ ነገሮች ከአንዱ ወደ ሌላው እየዘለሉ ከአቅሜ በላይ በሆነ ምክንያት “ታስፈልገናለህ” እየተባልኩ ነው ስመረጥ የነበረው፡፡ ብጠይቅ ችግር ነው፣ ስህተት ነው እያልኩ አይደለም፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ጠይቄ አላውቅም፡፡ አንተ ጋዜጠኛ ነህ፤ የቅንጅት አመራር የነበሩ አራት አምስት ሰዎችን ጠይቀህ፣ ሁለትና ሦስት ሰዎች “ልደቱ የሥልጣን ጥያቄ ነበረው” ካሉህ እኔ ተሳስቻለሁ ማለት ነው፡፡ ይቅርታም እጠይቃለሁ! ሊሉህ እንደማይችሉ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንግዲህ እኚህ ሰውዬ ትልቅ ሰው ናቸው፤ አቋማቸው ይጣመኝም አይጣመኝም ትግሉ ውስጥ ለከፈሉት ዋጋ አክብሮት አለኝ፡፡ ግን እንደዚህ ዓይነት ውሸት አልጠብቅም ነበር፡፡ ቅንጅትን ስንመሰርት ሊቀመንበር ሆኖ የመቀጠል ዕድል ነበረኝ፡፡ ግን “አይሆንም፤ የበሰሉ ሰዎች ቢመሩት ይሻላል” ብለን ነው ዶ/ር ኃይሉ እና ዶ/ር አድማሱን ከቤታቸው አምጥተን ስልጣኑን እንዲይዙትና እኛ የበታች ሆነን እንድንሰራ ያደረግነው፡፡ ይህንንም በተግባር አሳይተናል፡፡
ሎሚ፡- ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የቅንጅት ም/ሊመንበር ሆና ስትመረጥ፣ አንተ ለቦታው ራስህን አጭተህ ስለነበር በእጅጉ መበሳጨትህ ተሰምቷል፤ ይሕ ደግሞ በአንድ ሰው የተገለፀ ሳይሆን በርካታ የቅንጅት አመራሮች በተለያየ አጋጣሚ ደጋግመው የገለፁት ነው፤ ሥልጣን ካልፈለግክ ምን ነበር ያበሳጨህ;
ልደቱ፡- ቅድም እንዳልኩት ሰዎች እንዲሕ ሊሉ ይችላሉ፡፡ የሆነውን ነገር ግን ልነግርህ እችላለሁ፡፡ ወ/ት ብርቱካን በቅንጅት ውስጥ የተሰጣት ኃላፊነት አግባብ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እንድትመረጥ የተደረገው በድርጅታዊ አሠራር መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ወ/ት ብርቱካን ወደ ትግል እንድትመጣ ከማንም በላይ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እንደውም መመረጧ ደስ ብሎኝ በግንባር ቀደምነት ነው “እንኳን ደስ ያለሽ” ያልኳት፡፡ መድረክ ላይ የሆነው ይሄ ነው፡፡ የተወራው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ አዝናለሁ፡፡ እየተዳኘሁ ያለሁት በምሰራው ሥራ ወይም ባራመድኩት አቋም አይደለም፡፡ ሰዎች ስለኔ ባወሩት ወሬ ነው እየተዳኘሁ ያለሁት፡፡ ብርቱካን አልሞተችም አለች… እሷን ማነጋገር ትችላለህ፡፡
ሎሚ፡- ቅንጅት ውስጥ አለመግባባት በነበረበት ወቅት “የምሁራን ስብስብ ተፅዕኖ ሊፈጥርብን አይችልም” የሚል ንግግር ተናግረህ እንደነበር ታስታውሳለህ;
ልደቱ፡- አልገባኝም;…
ሎሚ፡- ወ/ት ብርቱካን እና ኢ/ር ኃይሉ ሻውል በቅንጅት አመራርነት ከተመረጡ በኋላ “የምሁራን ተፅእኖ ሊኖር አይገባም” ብለህ ነበር?…
ልደቱ፡- እንደዚያ ብዬ የተናገርኩበት ጊዜ አልነበረም፤ አላስታውስም፡፡ ግን በአጠቃላይ በሕይወትህ ምን ስህተት ሰርተሀል? ምን ዓይነት አመለካከት ነበረህ? ብትለኝ አንዱ ስህተት ለምሁራን የነበረኝ አመለካከት ነው፡፡ እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮፌሰርን፣ ዶክተርን… የፖለቲካ ሊቅ አድርጌ ነበር የማየው፡፡ ለዚያም ነው ኢዴፓን ስንመሰርት እኛ መስርተን እኛው መምራት የለብንም ብለን ምሁሮችን ከቤታቸው አምጥተን ኃላፊነት ላይ ያስቀመጥነው፡፡ ምናልባት ባላጋንነው ምሁር የሆነ ሰው የሚዋሽ አይመስለኝም ነበር፡፡ የስልጣን ጥማት ያለው አይመስለኝም ነበር፡፡ ሀገር ወዳድ ይመስለኝ ነበር፡፡ ሃቀኛ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ግን በጣም የተሳሳተ አመለካከት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን እንደዚህ አላስብም፡፡ ስለተማረና ስላልተማረ አይደለም፤ አንድ ሰው ምሁር ሆኖም የፖለቲካ ሴረኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ያልተማረም የፖለቲካ ሴረኛ አለ፡፡ በዚህ ረገድ ድሮ የነበረኝና አሁን ያለኝ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ግን አንተ እንዳልከው ቅንጅት ውስጥ ምሁራንን የተናገርኩበትን ጊዜ አላስታውሰውም፡፡
ሎሚ፡- ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር ተገናኝታችሁ ያወራችሁበት ጊዜ ነበር;
ልደቱ፡- ይመስለኛል፤ ሁለት ሦስት ጊዜ፡፡
ሎሚ፡- “እየሄድክበት ያለው መንገድ ጥሩ አይደለም፤ ለኢህአዴግ እየሰራህ ነው፤ ይህም ታውቋል፤ ስለዚህ ራስህን ከቦታው ብታገልል ጥሩ ነው” ያለህ ጊዜ ነበር;
ልደቱ፡- እስክንድር እንደዚህ ብሎኝ አያውቅም፡፡ ስለኔ ብዙ ነገር መፃፉን ግን አውቃለሁ፡፡ እስክንድር ፓርቲ አይደል መሪ አይደል፤ ከሂደቱ ውስጥ ውጣ አትውጣ ብሎ ሊያዘኝ የሚችልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እኔ እና እሱ በእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ዙሪያ አውርተን አናውቅም፡፡
ሎሚ፡-  ታዲያ “የአረም እርሻ” በሚለው መፅሐፍህ ውስጥ ሰፊ ቦታ ሰጥተህ ለምን ወቀስከው;
ልደቱ፡- ቅንጅት ውስጥ በነበርኩበት በተለይ ፓርላማ “ይገባ አይገባ” በሚባልበት ወቅት እሱ ያራምደው የነበረው አቋም ተገቢ አልነበረም፡፡ በእኔ እምነት ቅንጅትን ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንዲሄድ ከገፉት መካከል አንዱ የእስክንድር ጋዜጣ ነው፡፡ በዛ ምክንያት በመጽፌ ተችቼዋለሁ፡፡ እሱ በየሳምንቱ ይተቸኝ አልነበር? ታዲያ እኔ ብተቸው ምን ችግር አለው?
ሎሚ፡- እሱ የተቸህ እኮ አንተ የቅንጅት አመራር ሆነህ “ከኢህአዴግ ጋር በጐን እየሰራህ ነው” ብሎ ነው…
ልደቱ፡- ይሕን ለኔ… ነግሮኝ አያውቅም፡፡ እስክንድር እንደ አንድ ጋዜጠኛ ወይም እንደ አንድ የጋዜጣ ባለቤት የነበረው አቋም ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እሱ በቅንጅት ውስጥ ያራምደው የነበረው አቋም ስህተት ነው ብሎ እንደሚያምነው፣ እኔም እሱ ያራመደው አቋም ስህተት ነው ብዬ ፅፌያለሁ፡፡ ይህ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ በምትለው መልኩ ግን “ለኢህአዴግ እየሰራህ ነው” ብሎ የነገረኝ ጊዜ የለም፡፡
ሎሚ፡- ከቅንጅት ዕውቅና ውጪ ከአቦይ ስብሀት ነጋ ጋር የተገናኘኸው በምን ምክንያት ነው;
ልደቱ፡- የት ነው የተገናኘነው? አንተን ልጠይቅህ እስኪ፤
ሎሚ፡- በወቅቱ መረጃው የወጣው “መዝናኛ” በተሰኘ ጋዜጣ እንደሆነ አትዘነጋውም፤ ሁለታችሁ የተገናኛችሁትም በተጠቀሰው ዕለት ከቀኑ 11፡30 በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ቢሮ ውስጥ መሆኑም ተገልጿል…
ልደቱ፡- ዞሮ ዞሮ ይሄ ወሬ በተወራበት ወቅት ከአቶ ስብሀት ጋር አልተገናኘሁም፡፡ ይሄ ጉዳይ ሲወራም አቶ ስብሀት የተባሉትን ሰው በዓይኔም አይቻቸው አላውቅም ነበር፡፡ እንደ ማንም ሰው መፅሔት ላይ ፎቶግራፋቸውን ከማየት ውጪ አቶ ስብሓት ነጋ ቀይ ይሁኑ ጠይም፣ ረዥም ይሁኑ አጭር አላውቅም ነበር፡፡
ሎሚ፡- ከአቦይ ስብሃት ጋ አልተገናኛችሁማ?
ልደቱ፡- ይሔ ወሬ ሲወራ አንተዋወቅም፡፡ አቶ ስብሀትን በአካል ያየኋቸው ወይም ያገኘኋቸው ይሄ ወሬው ከተወራ ከሁለት አመት በኋላ ይመስለኛል፡፡ የቅንጅት ችግር ከተፈጠረ ከሁለት ዓመት በኋላ ፈረንሣይ ኤምባሲ አንድ የኮክቴል ግብዣ ላይ ነው ያገኘኋቸው፡፡ ግን ያኔ በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተን ቢሆን እንኳን ምንም የሚያሳፍረኝ ነገር የለም፡፡ ደስ የሚለኝ ነገር ነው፡፡ የሚያሳዝነኝ ግን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች (በገዢውም በተቃዋሚም ያለነው) በሀገር ጉዳይ ላይ እየተገናኘን አለመነጋገራችን ነው፡፡
ሎሚ፡- አንዳንድ ምንጮች ልደቱን ብአዴን/ኢህአዴግ አስቀድሞ ያዘጋጀው ሰው ነው ይላሉ፤ ተቃዋሚ መስለሕ ለማደናገር ወደ ፓርቲዎቹ እንደገባሕም ይነገራል፤ ያንተ ምላሽ ምንድነው;
ልደቱ፡- አሁን ለዚህ መልስ ብሰጥህ ምን ጥቅም አለው?… ኢህአዴግ በዚያ ደረጃ አዘጋጅቶ ወደ ተቃዋሚ ጐራ ሰርጌ እንድገባ ያደረገኝ ሰው ከሆነ የምሰጠው መልስ ይታወቃል፡፡ አይደለሁም ነው የምልህ፡፡ ግን ኢህአዴግን ለመጥቀም ከተፈለገ ለምንድነው ተቃዋሚ ውስጥ የምገባው? ኢህአዴግ ተቃዋሚ በዝቶበት አይደል እንዴ የተቸገረው፡፡ እንደዚህ ብለው የሚናገሩ ሰዎች መረጃቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት አሉት፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ብሆን ችግር የለውም፤ መሆን ብፈልግ ማለት ነው፡፡ የሚያሣፍርም ነገር የለውም፡፡ የኢህአዴግን የፖለቲካ አመለካከት አልወደውም፣ አላምንበትም እንጂ ባምንበት እኮ ኢህአዴግ እሆናለሁ፡፡ የሚያሳፍር ነገር አይደለም፡፡ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ብዙ ጓደኞች አሉኝ፤ ወንድሞች እህቶች አሉኝ፡፡ ግን አጋጣሚ ሆኖ የኔና የኢህአዴግ የፖለቲካ አመለካከት ስለማይጣጣም አልሆንኩም፡፡
ሎሚ፡- ቅንጅት በአንተ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ወስዶ ነበር፤ ወደ ስብሰባ አዳራሽ ስትገቡ ፍተሻው ሁሉንም የሚያካትት ቢሆንም መንስዔው ግን የአንተ ተጠርጣሪነት ነበር…
ልደቱ፡- ስለጉዳዩ ላስረዳህ፤ ፍተሻ ነበር፡፡ ያ የሆነው የቅንጅት አመራር የሚነጋገርባቸው አጀንዳዎችና ቃለ ጉባኤዎች በማግስቱ “ኢፍቲን” በሚባል ጋዜጣ ይወጣ ስለነበረ ነው፡፡ በኋላ ላይ በስልክ ወይም በዘመናዊ መሣሪያ የሚቀርፅ ሰው አለ ተባለ፡፡ ሁላችንም ሞባይላችንን ውጪ እየተውንና እየተፈተሽን እንግባ ብለን ተነጋግረን ወሰንን፡፡ ሞባይላችንን ውጪ እያስቀመጥን እየተፈተሽን መግባት ጀመርን፡፡ እንግዲህ በዚያ ጊዜ የሚጠረጠሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በተፈጠረው አለመግባባት መልቀቂያ ጠየቅኩኝ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ያንን ፊርማ ከፈረመ በኋላ ከሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነቴ ለቀቅኩ፡፡ እኔን ተክቶ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ገባ፡፡ ከአመራር ውስጥ ወጣሁ፡፡
ከወጣሁ በኋላም “ኢፍቲን” ጋዜጣ ያንን ነገር መዘገቡን ቀጠለ፡፡ ፍተሻውም ይካሄዳል፡፡ እኔ ብሆን ኖሮ እኔ ስወጣ መቆም ነበረበት፡፡ ግን ቀጠለ፡፡ ቃለ ጉባኤ የያዝንበት ምስጢር እየወጣ ስንቸገር እስቲ አንዳንድ ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮችን ሌሎቻችን በሌለንበት አራቱ የድርጅት መሪዎች ለብቻቸው ይነጋገሩ አልን፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ አራቱ የድርጅቱ መሪዎች (ዶ/ር ብርሃኑ፣ ዶ/ር አድማሱ፣ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል እና ዶ/ር አለማየሁ) ሰሜን ሆቴል ስድስተኛ ፎቅ አጀንዳ ይዘው ውይይት አደረጉ፡፡ አራቱ ብቻ ናቸው የተገኙት፡፡ የተነጋገሩበት አጀንዳ በነጋታው “ኢፍቲን” ላይ ወጣ፡፡
ታስታውስ እንደሆነ “ህብረት” ሲመሠረት ስብሰባው ላይ ለመካፈል ዋሽንግተን ዲሲ ሄጄ ነበር፡፡ ውይይት ስናደርግ አንዳንድ የሀሣብ ግጭቶች ተፈጠሩ፡፡ በእኛና በኢህአፓዎች መካከል ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ ሀሣብን በሀሣብ ማሸነፍ ሲገባቸው አሉባልታ አስወሩብኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አንድ የግል ጋዜጣ “አቶ ልደቱ የሕብረቱን ስብሰባ በቴፕ ሲቀዱ ተያዙ” ብሎ ዜና አወጣ፡፡ ስብሰባው አላለቀም፤ እዚያ ተቀምጠናል፡፡ በኋላ ተደውሎ ከኢትዮጵያ ተነገረኝ፡፡ በማግስቱ ስብሰባው ይቀጥል ስለነበር ወደ ስብሰባው ገብቼ “ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ተብሎ ተፅፏል፤ ይሄ ነገር ሀሰት መሆኑን አይታችኋል፤ ማስተካከል የለባችሁም ወይ?” ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ ኢህአፓዎች ይህንን ነገር ለመቀበልና ለማስተባበል አልፈለጉም፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ነገር ምላሽ አንሰጥም ተብሎ ታለፈ፡፡ ሀሳብን በሀሣብ ማሸነፍ ሲያቅታቸው እንዲህ ያስወሩብሃል፡፡
ሎሚ፡- ኢህአዴግ በወቅቱ አንተ በነበረህ ድጋፍ ተጠቅሞ በቅንጅት ውስጥ ልዩነት ፈጥረህ እንድትወጣ ግፊት አድርጓል ተብሏል፤ አንተ ስትወጣ ቅንጅት ለሁለት ይከፈላል ቢባልም ለግለሰብ ሳይሆን ለፓርቲ ቅድሚያ ተሰጥቷልም ተብሏል፤ ይህን ጉዳይስ እንዴት አየኸው;
ልደቱ፡- ሂደቱን የግል ጉዳይ አድርገህ አትየው፡፡ ልዩነቱ የተፈጠረው በእኔና በቅንጅት መካከል አይደለም፡፡ በኢዴፓና በቅንጅት ነው፡፡ እኔ ያራመድኳቸው ሀሳቦች የግል አቋሜ ሳይሆን በሙሉ ኢዴፓ ያመነባቸው ናቸው፡፡ ሌላ ውጫዊ አካል ተፅዕኖ አድርጐብን የያዝነው አይደለም፡፡ ያንጸባረቅነው መቶ በመቶ የምናምንበትን አቋም ነበር፡፡ ኢህአዴግ ስለገፋኝ ወይም ተፅዕኖ አድርጐብኝ አይደለም፡፡ አቋምህን ቀይር ተብዬ ተጠይቄም አላውቅም፡፡ ይሔ ልደቱን የኢህአዴግ ሰው ለማስመሰል የተደረገ ጉዳይ ነው፡፡
ከኢህአዴግ ጋር በፖለቲካ አቋም የምጣጣም ብሆን ኖሮ፣ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ አሉባልተኞች በደንብ አድርጌ አሳያቸው ነበር፡፡ ኢህአዴግ መሆን ምንም ማለት እንዳልሆነ አሳያቸው ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ግን ኢህአዴግ መሆን አልችልም፡፡ የሚመኙትን ምኞት በደንብ በተግባር አሳያቸው ነበር፡፡ ኢህአዴግ የሆኑ ጓደኞች አሉኝ፡፡ እነሱ ያላቸውን አስተሳሰብ አከብራለሁ፡፡ ምርጫቸው ነው፡፡ ከእነሱ ውስጥ አንዱ ብሆን ምንድነው ችግሩ; ከስድስት ሚሊዮን የኢህአዴግ አባል አንዱ ብሆን ምን ችግር አለው; ያ የፖለቲካ አመለካከት ነው፡፡ ተቃዋሚም ሆኜ የተቃዋሚው ሚና ካልጣመኝ ሀሣቤን ከቀየርኩ ኢህአዴግ መሆን እኮ መብቴ ነው፡፡ ትናንት ተቃዋሚ ነበርክና ዛሬ የኢህአዴግ አባል መሆን የለብህም የሚባል ነገር የለም፡፡ ትናንት ኢህአዴግ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ተቃዋሚዎች ሆነው የለ እንዴ? እነ አቶ ስዬና ዶ/ር ነጋሶ እኮ ትናንት የኢህአዴግ አባላት ነበሩ፡፡ በኋላ ተቃዋሚ ሆነዋል፡፡ ካመንኩበት እኔም ዛሬ ተቃዋሚ ሆኜ ነገ ኢህአዴግ ብሆን ምን ችግር አለው?…

“ልጆቼም እኔም ፍትህ እንሻለን”


saa

(የሟች ኢ/ር ጀሚል ባለቤት፤ ወ/ሮ ፋጡ የሱፍ)
“ለመጀመሪያ ጊዜ የባሌን መታመም በስልክ ነው የሰማሁት፡፡ ሌላ ጊዜ ወገቡን ያመው ስለነበር ያው ህመሙ ነበር የመሰለኝ። ተኝቷል ወደተባለበት አሚን ጀነራል ሆስፒታል በፍጥነት ስሄድ ያጋጠመኝ ሌላ ታሪክ ነው፡፡ ባለቤቴ ጭንቅላቱ ተጐድቷል፤ አንድ የቀረ የሰውነት ክፍል የለውም፡፡ ተደብድቧል፡፡ ራሱን ስቶ እየቃዠ ነበር ያገኘሁት (… ከፍተኛ ለቅሶ …) ነገሩን ሳጣራ በብዙ ሰዎች ተደብድቦ ከቡታጅራ ነው ወደ አሚን ጀነራል ሆስፒታል የመጣው”
ይሄን የተናገሩት ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም የ“ሊቃ” በዓልን ለማክበር ወደ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ፣ ሚኬኤሎ ገበሬ ማህበር፣ መልካሜ መስጊድ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ሄደው፣ ባደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው ያለፈው የኢ/ር ጀሚል ሀሰን ባለቤት ወይዘሮ ፋጡማ የሱፍ ናቸው፡፡
በጉራጌ ዞን በመስቃን ወረዳ በየወሩ የሚከበረውን “ሊቃ” የተሰኘ ሀይማኖታዊ በዓል ለማክበር ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሱማሌ ተራ ከሚገኘው መስጊድ ተነስተው ከ50 በላይ ሰዎች ወደ ስፍራው ተጉዘው ነበር፡፡ በእለቱ ሚኬኤሎ በተባለው አካባቢ መልካሜ መስጊድ ደርሰው ስርዓቱን ለመከታተል ገና እንደገቡ እጅግ በርካታ ዱላ የያዙ ሰዎች ከአዲስ አበባ የሄዱትን ሰዎች መደብደብ ጀመሩ። አገር ሰላም ብለው የሄዱት እንግዶች፤ በአካባቢው ሰው የዱላ ውርጅብኝ ሲወርድባቸው ያመለጠው አመለጠ፤ የተጐዳው ተጐዳ፤ ነገር ግን ኢ/ር ጀሚል ማምለጥ ባለመቻላቸው ዱላው ሁሉ ሰውነታቸው ላይ አረፈ። ጭንቅላታቸውም ላይ ድንጋይ ተጫነ፡፡ በሞትና በህይወት መሀል ሆነው ከአዲስ አበባ በተላከ አምቡላንስ አሚን ጀነራል ሆስፒታል ገቡ፡፡
ህይወታቸውን ለማትረፍ ዶክተሮችና ነርሶች አቅምና እውቀታቸውን እስከመጨረሻው አሟጠው ቢጠቀሙም የኢ/ር ጀሚል ህይወት ተስፋ ሰጪ አልነበረም፡፡ በአስቸኳይ ወደ ቱርክ ሄደው እንዲታከሙ የአሚን ጀነራል ሆስፒታል ዶክተሮች ትዕዛዝ አስተላለፉ። ጉዞ ወደ ቱርክ ሆነ፡፡ ቱርክ በደረሱ በሶስተኛው ቀን ኢ/ር ጀሚል ሀሰን ይህቺን አለም እስከወዲያኛው ተሰናበቱ። “በሰው አገር ደህና ሰውነት የሌለውን፣ በዱላ ባዘቶ የሆነውን የባሌን አስክሬን ይዤ ግራ ገባኝ፤ ልጆቼን አሰብኳቸው፤ ለልጆቼ አባታቸው ምን ማለት እንደሆነ የማውቀው እኔ ነኝ” ይላሉ፤ የአቶ ጀሚል ባለቤት ወ/ሮ ፋጡማ የሱፍ፡፡ “ልጄ ኪናን ጀማል በትምህርቱ ጐበዝ ነበረ፤ ኢትዮጵያን ወክሎ ቱርክ በመሄድ ተወዳድሮ አንደኛ በመውጣቱ ከኢስታምቡል ፓርላማ ሽልማት ተቀብሏል፤ አሁን ግን በአባቱ ሞት የተነሳ መማር አልቻለም” ብለዋል፤ ወ/ሮ ፋጡማ፡፡
የድርጊቱ መንስኤ
ወልቄጢ አካባቢ “ቃጥባሬ” የተሰኘ መስጊድ ይገኛል፡፡ መስጊዱ በኢ/ር ጀሚል ገዳይ ቅድመ አያት በሀጂ ኢሳ እንደተሰራ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ሀጂ ኢሳ በአካባቢው እስልምናን ያስፋፉ አስተማሪና በአካባቢው ህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ሼክ እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ፡፡ ሀጂ ኢሳ ካለፉም በኋላ ልጃቸው ሻለቃ ሱልጣን ሀላፊነቱን ተረክበው የእስልምናን እምነት በትክክለኛው መንገድ ሲያስተምሩ፣ የተጣላን ሲያስታርቁ፣ ለታመመ ሲፀልዩና ሲያድኑ የቆዩ የሀይማኖት አባት እንደነበሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአካባቢው ሰዎች ይናራናሉ፡፡ እኚህ አባት በስልጤ፣ ጉራጌ፣ በሶዶ ወረዳ የተለያዩ መስጊዶችን በማሰራት እምነቱ በትክክለኛው መንገድ እንዲቀጥል የራሳቸውን አሻራ ጥለው ማለፋቸውን ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ፡፡
እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለፃ፤ ሀይማኖቱ እየተበላሸና ሌላ መልክ እየያዘ የመጣው ከሻለቃ ሱልጣን ልጅ እና ከልጅ ልጃቸው በኋላ ነው፡፡ በተለይ የልጅ ልጃቸው አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፤ ከቅድመ አያቶቻቸውና ከአያቶቻቸው የተረከቡትን የእምነት ስርዓት ወደ ጐን በመተው፣ “ከአላህ ይልቅ እኔን አምልኩ” በሚል ወደ ጥንቆላና ባዕድ አምልኮ ቀየሩት ይላሉ፤ ነዋሪዎቹ፡፡ ይህን ጉዳይ አጥብቀው ከሚቃወሙት ውስጥ ደግሞ የሰልማን ሰይድ ፋሪስ አጐት በድሩ ሱልጣን አንዱ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በድሩ ሱልጣን፤ የሰልማን ሰይድ ፋሪስ የአባታቸው ወንድም (አጐታቸው) ናቸው፡፡
“ይሄ ነገር አይሆንም፤ ሰው ሁሉ ማመን ያለበት በፈጣሪው በአላህ ነው፤ ወደ አላህ መንገድ መመለስ አለብህ እያልኩ ሰው ሁሉ እሱን እንዲያመልክ የሚያደርግበትን መንገድ እቃወም ነበር፤ በዚህ ነው ሊገድለኝ የነበረው” ይላሉ፤ ከሞት የተረፉት አጐቱ አቶ በድሩ ሱልጣን፡፡ መጀመሪያ ሊገደሉ እቅድ የተያዘባቸው አጐቱ አቶ በድሩ ሱልጣን እንደነበሩና ግንቦት 19 ቀን 2004 ዓ.ም እራሱን “የሀይማኖት መሪ” እያለ የሚጠራው አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፤ ለታናሽ ወንድማቸው እና ለተከታዮቻቸው መመሪያ ሲያስተላልፉ ሰምቻለሁ ብለዋል – አንድ የአይን እማኝ፡፡
የቡታጅራና የአካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ ህዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም (ኢ/ር ጀሚል ሐሰን ከተገደሉ ከስድስት ወራት በኋላ) የግድያው ዋና መሪ፣ አዘጋጅና አዛዥ እንዲሁም የግድያው ቀድሞ ጀማሪዎች የሀይማኖት መሪ ናቸው በተባሉት:- ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ሱልጣን፣ ወንድማቸው ነሲቡ ፋሪስ ሱልጣን፣ ወልዩ ቦንሰሞና ሁሴን አብደላ በተባሉት ተከሳሾች ላይ በሶስት ተደራራቢ ወንጀል ክስ ተመስርቶ እንደነበር የአቃቤ ህግ መዝገብ ያስረዳል፡፡ ክሱም ከባድ የነፍስ ግድያ፣ በከባድ የነፍስ ግድያ ሙከራ እና ታስቦ የሚፈፀም የንብረት ማውደም የሚል ሲሆን ተከሳሾቹ የፈፀሙት ወንጀል፤ (በሁለት ተደራራቢ ክሶች) ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚደርስ ፍርድ የሚያሰጥ ቢሆንም በቅጣት ማቅለያ ከ20 እስከ 11 ዓመት እስር ተፈረደባቸው፡፡ ክስ የቀረበባቸው 22 ሰዎች ቢሆኑም ሁለቱ አቃቤ ህግ አላስመሰከረባቸውም በሚል በነፃ ሲሰናበቱ፣ 20ዎቹ እንደየጥፋታቸው መጠን እስር ተፈረደባቸው – ከ11-20 ዓመት፡፡
የቡታጅራና አካባቢው ነዋሪና አቃቤ ህግ ግን በፍርዱ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ጥፋተኞቹ ሞት እና እድሜ ልክ እስር ሊፈረድባቸው ሲገባ ፍ/ቤቱ የሰጠው ብያኔ አግባብ አይደለም ያለው አቃቤ ህግ፤ ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆሳዕና ምድብ ችሎት ይግባኝ ጠየቀ፡፡
በቡታጅራና አካባቢው የህግ ባለሙያ የሆኑትና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያውቁ ጠቁመው፤ ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች በፊናቸው ምድብ ችሎት ሆሳዕና እያለ፣ እነሱ ግን ሀዋሳ በመሄድ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ማለታቸው አግባብ አልነበረም ይላሉ፡፡ የሆነ ሆኖ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የጥፋተኞችን ፋይል ከፍቶ ጉዳያቸውን ካየ በኋላ፣ የቡታጅራና አካባቢው ጠ/ፍ/ቤት አቃቤ ህግ ሆሳዕና ምድብ ችሎት ይግባኝ ያለበትን መዝገብ አጣምሮ ለማየት የሟች ጉዳይ መዝገብም ወደ ሀዋሳ ተዛወረ፡፡ የጉዳዩ ሂደት መዝገብ እንደሚያሳየው፤ በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት በአቶ ታረቀኝ አበራ አይዶ እና በሌሎች ዳኞች የታየው የሁለቱ ወገኖች ይግባኝ የሟችን መዝገብ በዝርዝር ሳይመለከት እንዲሁም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ የተባሉበትን ከፍተኛ የነፍስ ግድያ ወንጀል ተራ አምባጓሮ ወደሚለው በመለወጥ፣ “ከአዲስ አበባ ሊቃችንን ሊያበላሹ ይመጣሉ፤ ዱላ (ሽመል) ይዛችሁ ደብድቧቸው፣ ይህን ያላደረገ ከእኔ ጋ እንደተጣላ ይቁጠረው” የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፍ ግድያውን በቀጥታ መርቷል በሚል 14 ዓመት የተፈረደበትን ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፤ አቃቤ ህግ ማክበጃ አላቀረበም በሚል በቅጣት ማቅለያ ወደ አምስት አመት፣ የግድያውን ሂደት ዱላ በማሳረፍ አስጀምሯል የተባለውና የሰልማን ሰይድ ፋሪስ ታናሽ ወንድም የሆነው ነሲቡ ፋሪስ ከ19 ዓመት ወደ ዘጠኝ አመት ሲቀነስላቸው፤ የሌሎቹም ከ13 እና ከ11 ዓመት ወደ አንድ አመት ከስምንት ወር በመቀነሱ በጠቅላይ ፍ/ቤቱ ውሳኔ፣ እጃቸው ከተያዘ ጀምሮ አመት ከስምንት ወር ያለፋቸው 14 ሰዎች በነፃ ሊለቀቁ ችለዋል። ይህም ውሳኔ በሟች ቤተሰብ ዘንድ ለቅሶና ዋይታን ፈጥሯል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸውና ሂደቱን ሲከታተሉት እንደነበር የገለፁልን የህግ ባለሙያ፤ ጉዳዩን የስር የቡታጅራና አካባቢው ፍ/ቤት፤ ተንትኖ እንዳየው፤ ከ50 በላይ የሰነድና ከ50 በላይ የሰው ማስረጃ ቀርቦለት በትክክል መወሰኑን ይናገራሉ፡፡ ይህን ውሳኔ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ በአንድ አንቀፅ መሻሩ ፍትህ መዛባቱን እንደሚያሳይ የህግ ባለሙያው ገልፀዋል፡፡
“አጠቃላይ የሂደቱ መዝገብ እጄ ላይ ስላለ በደንብ ተመልክቼዋለሁ” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኢፌዲሪን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ የጣሰ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ባለሙያው “ስህተት” ነው ያሉት 539 1(ሀ) ከፍተኛ የነፍስ ግድያ ወንጀል ወደ 540 ተራአምባጓሮ መቀየሩን ነው። ከተቀየረም የተቀየረበት አጥጋቢ ምክንያት መኖር ነበረበት፤ ነገር ግን “ይህን አልተቀበልኩም፣ ይሄ አያስኬድም” እያለ ጠ/ፍ/ቤት የወሰነው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት እንዳለበት በግልፅ ያሳያል ብለዋል፡፡
የሟች ባለቤት ወ/ሮ ፋጡማ የሱፍ በበኩላቸው፤ በጠ/ፍ/ቤቱ የተሰጠው ውሳኔ በእርሳቸውም ሆነ በልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ሀዘን እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡ “አባቴን የገደለው ሰው አምስት አመት ከተፈረደበት እኔም እሱን ገድዬ አምስት አመት መታሰር አያቅተኝም” በሚል ልጄ ወደበቀለኝነት ሀሳብ ገብቷል ሲሉ “የፍትህ ያለህ” ብለዋል፡፡ “እኔም ሆንን ልጆቹ ኢትዮጵያዊያን ነን ልጆቼን የት ሄጄ ላሳድግ የልጄን ሀዘንና የበቀለኝነት ስሜት እንዴት ነው የማስወግደው?” በማለት ያለቅሳሉ፡፡
“ትክክለኛ ፍርድ አገኛለሁ ብዬ ከአዲስ አበባ ሀዋሳ 35 ጊዜ ተመላልሻለሁ፤ እዛም ደርሼ ለሌላ ጊዜ ተዛውሯል፣ ከሰዓት ነው እየተባልኩ ልጆቼንና ስራዬን ጥዬ ተንከራትቻለሁ” ያሉት ወ/ሮ ፋጡማ፤ በውሳኔው በጣም ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ “የጠ/ፍ/ቤቱን ፕሬዚዳንት አነጋግሪ ተብዬ አቶ ታረቀኝን እያለቀስኩ ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር” ያሉት ወ/ሮዋ፤ “ትክክለኛ ፍርድ ታገኛለሽ፤ መዝገቡ በእኔ እጅ ነው” ብለውኝ ስጠብቅ፣ ጭራሽ 14 ሰዎች በነፃ ሲለቀቁ፣ የነፍሰ ገዳዮቹ ቅጣት ወደ አምስትና ዘጠኝ አመት መቀነሱ አሳዝኖኛል ብለዋል፡፡
“ውሳኔው ከአድልዎ፣ ከአምቻ ጋብቻ የፀዳ ነው”
አቶ ታረቀኝ አበራ
በጉዳዩ ዙሪያ ሀዋሳ ቢሯቸው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አበራ፤ “ጉዳዩን በደንብ አውቀዋለሁ፤ ውሳኔውም በትክክል ታይቶ ተፈትሾ የተወሰነ ከአድልዎ፣ ከአምቻ ጋብቻ የፀዳ ነው” ብለዋል፡፡ ሆሳዕና ምድብ ችሎት እያለ፣ አቃቤ ህግም በሆሳዕና ይግባኝ ብሎ ሳለ ጥፋተኞቹ ወደ ክልሉ ጠ/ፍ/ቤት መጥተው ይግባኝ ሲሉ ፋይል ተከፍቶ መስተናገድ ነበረባቸው ወይ? በሚል ላነሳነው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “መንግስት በየአቅራቢያው ምድብ ችሎቶችን የከፈተው ሰዎች የጊዜ፣ የገንዘብና መሰል ብክነቶች ለመከላከል ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሆኖም ለየት ያሉ ጉዳዮች ሲመጡ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፋይል እንደሚከፍት ገልፀው፤ ይሄኛውን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው ሀይማኖታዊ ይዘት ስላለው ነው ይላሉ፡፡ አንቀፁ ከ539 /ሀ/ (1) እንዴት ወደ 540 (ተራ አምባጓሮ) ወደሚለው ለምን ተቀየረ? በሚል ላቀረብነው ጥያቄም፤ “ጉዳዩ የተፈፀመው በሀይማኖት ቦታ ሆኖ በድንገት በተነሳ ግርግር እንጂ የታሰበበት እንዳልሆነ ፍ/ቤቱ አጣርቷል፤ በዚህም ውሳኔ ሰጥቷል” ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ የስር የቡታጅራ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ተከታዮቹን በመልካሜ መስጊድ በ19/09/2004 ዓ.ም ሰብስቦ “ነገ-ከአዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች አሉ፤ የሊቃ ስርዓቱን ለማበላሸት ስለሆነ ጅሀድ (ጦርነት) እናውጅባቸዋለን፡፡ ሁላችሁም ዱላ ሽመል ይዛችሁ ቀጥቅጣችሁ ግደሉ” ስለማለቱ 50 የሰው፣ 50 የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ “አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ከዚህ ቀደም ብዙ የግድያ ሙከራዎች አድርጓል” የሚሉት አንድ የቡታጅራ አካባቢ ነጋዴ ስለተፈጠረው ነገር በደንብ እንደሚያውቁና በቅድሚያም ድርጊቱን እንደሚያወግዙ በመግለፅ ነው አስተያየታቸውን የጀመሩት፡፡ ከዚህ በፊት ወንጀለኛው (ሰልማን ሰይድ ፋሪስ) በሀይማኖት ሽፋን ህብረተሰቡን ያለ አግባብ “የሀይማኖት መሪ ነኝ” በማለት ራሱን ሰይሞ ምንም የሀይማኖት ምልክት በሌለበት እየበዘበዘ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ “ሰውንም ወዳልተፈለገ እምነትና ጥንቆላ ከቶታል” የሚሉት ነጋዴው፤ ይህ ሰው ከአቶ ጀሚል በፊት በጠራራ ፀሀይ ሁለት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላይ ሽጉጥ መተኮሱን፣ በዚህም ክስ እንደተመሰከረበት ጠቁመው “የሀይማኖት መሪ ነው” በሚል በነፃ መለቀቁን ይናገራሉ። “የወረዳው ይህን ያህል ሽፋን መስጠት አሁን ወደ ነፍስ ግድያ አሸጋግሮታል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሊቃ ስርዓት በሰላም ነው በየወሩ ሲከበር የነበረው ያሉት እኚህ ግለሰብ፤ “ከአዲስ አበባ የሚመጡ ስርዓቱን የሚያበላሹ ሰዎች ስላሉ በሰላም እንዳይመለሱ በዱላ ደብድባችሁ ግደሉ” የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉንና በዓሉ በሚከበርበት ቀን እርሱ በበዓሉ ላይ አለመገኘቱን፣ ከዚያ በፊት ግን ከሊቃ ስርዓቱ ቀርቶ እንደማያውቅ መስክረዋል፡፡
“አሁንም ቢሆን ማረሚያ ቤት ሆኖ በየጊዜው በመኪና እየታጀበ ወደ ቤቱ ይሄዳል፣ ኦሮሚያ ክልል ላይ የእርሻ ማሳ አለው፤ እርሱን ሊያሰራ ይሄዳል” ያሉት ግለሰቡ፤ ይህ የሚደረግለት ሽፋን ለቀጣይ ነፍስ ግድያ ያበረታታዋል ብለዋል፡፡ “ድብደባውን እና ግድያውን ፈፅመው ሲመለሱ ሌላው ተባባሪ የዛሬው ግንቦት 20 የድል ቀን ነው በደንብ አክብረነዋል እባክሽ ቅቤ ቀቢኝ ብሎ ለዋርሳው ሲናገር በጆሮዬ ሰምቻለሁ” የሚሉት ግለሰቡ፤ “ይህ ሰው ታስሮ ነበር፤ በይግባኙ ሂደት ተለቆ ወጥቷል ግን ድጋሚ እየተፈለገ ነው፤ ለአካባቢው ስጋት ሆኗል” ብለዋል፡፡
“በአካባቢያችን አንድ አርሶ አደር በቀን 60 ብር እየተከፈለው በሚሰራበት ወቅት ብዙ አርሶ አደሮች በነፃ እርሱን ሲያገለግሉ ይውላሉ” በማለትም አክለዋል፡፡
“በድሩ ሱልጣን የተባለው አጐቱ ሌሎች እንግዶችን ከአዲስ አበባ ይዞ እንደሚመጣ ያውቅ ነበር፤ አቶ በድሩ የተማረ በመሆኑ አጥብቆ ይቃወመዋል፤ ህዝቡን የሚበዘብዝበትን መንገድ እንዳያጣ ነው አጐቱን ግደሉት ያለው” ብለዋል፡፡ ሆኖም የአላህ ፈቃድ ሆኖ አቶ በድሩ ተደብድቦ ሲተርፍ፣ ኢ/ር ጀሚል ለሞት በቃ ብለዋል፡፡
“ወንጀሉን ፈፃሚውም ሟቹም ቤተሰቤ ነው ያለው ሌላ የቡታጅራ ከተማ ወጣት ነዋሪ፤ አጐቱ በድሩ ሱልጣን የሊቃን ስርዓት ከማክበር ባሻገር ከቃጥባሬ እስከ ወልቂጤ ያለ 12 ኪ.ሜ ኮረኮንች መንገድ በአስፋልት ለመቀየር አስቦ፣ ሟችን ጨምሮ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎችን ከአዲስ አበባ ይዞ እንደሚመጣና መንገዱን በተመለከተም ከህዝቡ ጋር ምክክር ለማድረግ ቀጠሮ አስይዞ እንደነበር ወጣቱ ይናገራል፡፡ “እወጃውን በግንቦት 19 አውጆ፣ ለበዓሉ ቀረ፤ ከዛን በፊት ቀርቶ አያውቅም” የሚለው ወጣቱ እነዚህ ሰዎች አገር ሰላም ብለው ሁለት ሚኒባስና አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ ይዘው ግንቦት 20 ቀን 2004 በስፍራው መገኘታቸውን ገልጿል፡፡ “በዋና ገዳይነት ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኘውታናሽ ወንድሙ ነሲቡ ሱልጣን “የተባሉት ሰዎች መጥተዋል ተነሱ” በሚል ድብደባውን መጀመሩንና ከሞቱት ግለሰብ ውጭ 19 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ወጣቱ ገልጿል።
የገዳይ የቅርብ ዘመድ እንደሆኑ የነገሩን ሌላው አዛውንት የአካባቢው ነዋሪ፤ ወንጀለኛው በእናቱ በኩል ዘመዳቸው እንደሆነ ገልፀው፤ “አንድ ጊዜ ወፍጮ ቤትህ በደንብ እንዲሰራ፣ ንግድህ እንዲቃና ከሱዳን ያስመጣሁት አዋቂ ስላለ 30 ሺህ ብር ከፍለህ መድሀኒት ላሰራልህ ብሎኝ እምቢ ብየዋለሁ” ብለዋል፡፡ ወንጀለኛው ጥንቆላ ውስጥ መግባቱንና ህዝቡን እያንቀጠቀጠ ገንዘብ እንደሚቀበልም ነዋሪው ተናግረዋል፡፡
የቡታጅራና አካባቢው ነዋሪዎች በእስር ላይ ስለሚገኘው ፍርደኛ፤ ሲናገሩ “እስር ቤቱ ለእርሱ መዝናኛው ነው፤ ድንኳን ተጥሎለት አሁንም ከህዝቡ ገንዘብ እየሰበሰበ ነው፤ ከእስር ቤት እየወጣ በየጊዜው ወደ ቤቱ ይሄዳል፣ “ወራ” የተባለውን የራሱን ሀይማኖታዊ ስርዓት ከማረሚያ ቤት ወጥቶ እቤቱ ነው ያከበረው፤ እርሻውን 50 ኪ.ሎ ሜትር እየሄደ ያሰራል፤ በየጊዜው ከማረሚያ ቤቱ 18 ኪ.ሜትር ወደሚርቀው ቤቱ ይሄዳል፤ ከፍተኛ ሀዘንና ችግር ቢከሰት እንኳን ከማረሚያ ቤቱ ሰባት ኪሎ ሜትር ራዲየስ መራቅ በህጉ አይፈቀድም፤ ለዚህ ሰው ሽፋን የሚሰጥበት ሁኔታ ለአካባቢው ስጋት ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡
“ከፖሊስ ጣቢያ በህገ-ወጥ መንገድ ነው ያመጣነው”
ኮማንደር ወንደሰን አበበ
የቡታጅራ ማረሚያ ተቋም ሀላፊ ኮማንደር አበበን በማረሚያ ተቋሙ ተገኝተን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ “በ2004 በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሰው የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ሰዎች አሉ” በማለት ነው ጥያቄያችንን መመለስ የጀመሩት፡፡ በነፍስ ግድያው ወደ ማረሚያ ቤት የመጡት 19 ሰዎች እንደነበሩ ጠቁመው 14ቱ በአመክሮ እንደተፈቱ ኮማንደሩ ገልፀዋል፡፡ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ካሉት መካከል አንዳንዶቹ እንደፈለጉት እየወጡ ይገባሉ የሚባለውን በተመለከተ ሲናገሩም፤ “የህግ ታራሚዎች ገና ወደ ማረሚያ ቤት እንደገቡ በርካታ ማህበራዊ ችግሮች እንዳሉባቸው ይናገራሉ” የሚሉት የተቋሙ ሀላፊ፣ ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ ቤተሰባቸውን ሳያረጋጉ፣ ማረሚያ ቤት እንደሚገቡ ጠቅሰው፤ ከዚህ አንፃር ህጉ ፈቃድ ይሰጣቸዋል ይላሉ፡፡ “ይህ ማለት ግን በየቀኑ ይወጣሉ ማለት አይደለም” ያሉት ኮማንደሩ፤ “በርካታ ንብረት በትኜ ነው የመጣሁት” የሚል ማመልከቻ ካቀረቡ በኋላ ጉዳዩ ተጣርቶ አጃቢ ተመድቦላቸው ሄደው እንደሚመጡ፣ ይህን የሚፈቅድ ህግ እንዳለም አብራርተዋል፡፡ ከኢ/ር ጀሚል ግድያ ጋር በተያያዘ በተቋሙ በእርምት ላይ የሚገኙት ሰልማን ሰይድ የአያያዝ አግባብ ሲያስረዱም፤ ሰውየው የልብ ህመም ስላለባቸው በየሶስት ወሩ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ እንደሚመላለሱ ገልፀው፣ ይህ የሀኪም ትዕዛዝ እና የጤና ጉዳይ ስለሆነ የግድ መሄድና መታከም እንዳለባቸው፤ ምንም ማድረግም እንደማይቻል ኮማንደሩ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
“የሰልማን ሰይድ ፋሪስን ጉዳይ በተመለከተ ውጭ ይወጣሉ በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ከተለያዩ አካላት ይቀርብልናል” ያሉት ኮማንደር ወንድወሰን፤ ይህንንም በትክክለኛው መንገድ እየመለሱ እንደሚገኙ፣ ጤንነታቸውን በተመለከተና የመኝታን ጉዳይም ጭምር ዶክተሮች በሰጡት መመሪያ መሰረት ለብቻቸው እንዲተኙ መደረጉን ያብራራሉ፡፡
ለሰልማን ሰይድ ከህጉ ውጭ የተለየ ነገር አልተፈቀደለትም ይላሉ የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ፤ አንድ የህግ ታራሚ ወላጆቹና ቤተሰቦቹ ቢሞቱበት 6 ኪ.ሜ ራዲየስ ድረስ ሄዶ እንዲቀብር የማረሚያ ቤቱ አሰራር ይፈቅዳል ያሉት ኮማንደሩ፤ ቡታጅራ ሆስፒታል የተኛ የቅርብ ቤተሰብ (ዘመድ) ካለውም ጠይቆ እንዲመጣ ፈቃድ እንዲሰጥ ህጉ ያዛል ብለዋል፡፡ “እርግጥ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ በአንድ ወቅት እህል መሰብሰብ አለብኝ፣ ገንዘብ ያለበትንም ለባለቤቴ ልንገር ብለውን ፈቅደንላቸው ሄደው መጥተዋል፤ ከዚህ የዘለለ ግን እንደ ውሀ ቀጂ የሚመላለሱበት ጉዳይና የተለየ እድል የሚሰጥበት የህግ አግባብ የለም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኦሮሚያ ክልል ሄደው ማሳ ያሰራሉ፣ “ወራ” የተባለውን የራሳቸውን የሀይማኖት በዓል በቤታቸው ያከብራሉ፤ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ዳስ ተጥሎ ገንዘብ ይሰበስባሉ በሚል በታራሚው ላይ የሰማነውን መረጃ የጠቀስንላቸው ኮማንደሩ ሲመልሱ፣ “ኦሮሚያ ድረስ የሚሄዱበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም በነፍስ ግድያ የገቡ ሰው ናቸው በቀል ስለሚኖር በሰው ጉዳት ሊደርስባቸውም ጉዳት ሊያደርሱም ይችላሉ በሚል የማረሚያ ተቋሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ሌላ ታራሚ፤ ገንዘቤን ልሰብስብ፤ ቤተሰቤን ላረጋጋ ቢል ይፈቀድለት እንደሆነ ጠይቀ ናቸውም፤ ድንገት ተይዞ ለገባ ታራሚ ህጉ ለአንድ ቀን ብቻ እንደሚፈቀድ ተናግረዋል፡፡
ዳስ ተጥሎላቸው ገንዘብ ይሰበስባሉ የሚለውን በተመለከተም፤ እኔ በማረሚያ ተቋሙ ስሰራ 11 ዓመቴ ነው፤ በዚህ አመት ውስጥ በቀን ብዙ ጠያቂ መጣ ከተባለ 10 ወይም 15 ሰው ነው” ያሉት ሃላፊው፤ እኚህ ሰው ወደማረሚያ ቤቱ ከመጡ በኋላ በቀን ከ100 እስከ 250 ሰው ወደማረሚያ ቤቱ መምጣት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ የታራሚ መጠየቂያም በጣም ጠባብ በመሆኑ የግድ ዳሱ መጣል ስለነበረበት በላስቲክ ዳስ ተሰርቶ እንዲጠየቁ መደረጉን ገልፀው፤ “ይህንን ያደረግነው የሌሎች ታራሚዎችን ጠያቂዎች እድል ላለመንፈግ ነው” ያሉት ኮማንደሩ፤ ሰውየው ገንዘብ ይሰብስቡ አይሰብስቡ ማረሚያ ተቋሙን አይመለከተውም ብለዋል፡፡ ጠያቂው ከጠየቀ በኋላ ገንዘብ ሰጥቷቸው እንደሚሄድ በመግለጽ። “ከዚህ በተረፈ ከሌሎች ታራሚዎች የተለየ እድልና ቅድሚያ ለእርሳቸው የምንሰጥበት ምክንያት የለም፤ ዳሱንም ቢሆን ተቋሙ ሳይሆን ራሳቸው ታራሚው ናቸው ያዘጋጁት፡፡” ብለዋል፡፡ (በነገራችን ላይ በሰማያዊ ላስቲክ የተጣለውን ዳስና የተነጠፈውን ጂባ ምንጣፍ በስፍራው ተመልክተናል፡፡)
“እንኳን የተለየ እድል ልንሰጣቸው ከፖሊስ ጣቢያም ያመጣናቸው በህገ ወጥ መንገድ ነው” ያሉት ኮማንደሩ፤ ግድያው ራሱ የተፈፀመው በሃይማኖቱ የተነሳ መሆኑን፣ ሟችም አደጋው የደረሰባቸው በሰው ማመን የለብንም በሚል መሆኑ እንደሚታወቅ ገልፀው፣ “ታራሚው ከአያቴ፤ ከአባቴ የወረስኩት ነው የሚለውን እምነት እንዲያራምድ እንዴት ወደቤቱ እንልከዋለን” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እንደውም ከታራሚው ጋር የተፈጠረ ግጭት እንደነበር የሚያስታውሱት ሃላፊው፤ በአንድ ወቅት በማረሚያ ተቋሙ ውስጥ ከብት ሲታረድ “ሼኩ ያረዱትን ሳይሆን እራሳችን ያረድነውን ነው የምንበላው” በሚል ከታራሚው ጋር በነፍስ ግድያው ተፈርዶባቸው የመጡት ችግር ፈጥረው እንደነበረና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቄራ እየታረደ ስጋ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ታራሚው ከዚህ በፊት በሰዎች ላይ ሽጉጥ ስለመተኮሳቸው፣ ብዙ ጊዜ ስለመከሰሳቸውና በማረሚያና በፖሊስ ጣቢያ ሽፋን ይሰጣቸዋል ስለመባሉ ያውቁ እንደሆነ ጠይቀናቸው፤ ሰውየው ወደማረሚያ ቤቱ የገቡት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ጠቅሰው ቀደም ሲል፣ ፖሊስ ጣቢያ ገብተው ይሆናል እንጂ ማረሚያ ቤት አልመጡም ብለዋል፡፡ “እርግጥ እኛም ከፖሊሶች እኒህን ታራሚና ሌሎች 19 ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ነው የተቀበልናቸው ያልኩሽም፤ ገና ሳይፈረድባቸው ፖሊስ ጣቢያ እያሉ ሰዎችን ማነሳሳትና መሰል ድርጊቶችን ይፈጽሙ ስለነበር፣ ነገሩ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይዞር በመፍራት ነው ፍርድ ከማግኘታቸው በፊት ያመጣናቸው” ብለዋል፡፡
ድሮ አሜሪካም ሆኜ እዚህም ከመጣሁ ጀምሮ ሰልማንና ወንድሞቹ የሚያራምዱት እምነት አይስማማኝም ነበረ “የግድያው መንስኤም ይሄው ይመስለኛል” የሚሉት አቶ በድሩ፣ የጀሚል ሞት ግን የእድሜ ልክ ሀዘን እንደሆነባቸው በሀዘን ገልፀዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ነፍሰ ገዳዮቹንና ግብረአበሮቻቸውን በይግባኙ የቀነሰላቸው የእስራት ጊዜና 14 ሰው በነፃ የለቀቀበት መንገድ ለኢ/ር ጀሚል እና ለቤተሰቦቹ፤ ለእኛም ጭምር ሁለተኛ ሞት ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ለሰበር ሰሚ ይግባኝ ቢጠይቅም ይግባኙ የዘገየ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ፋጡማ፤ ወደ ሰበር ችሎት ጉዳዩ ከመጣ በኋላ 14ቱን ሰዎች ያስቀርባቸዋል በሚል ሰበር ችሎቱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ትዕዛዝ ቢሰጥም የተፈቱት 14 ሰዎች ግን ራሳቸውን በመሰወራቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ ገልፀውልናል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለሶስተኛ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለጥቅምት 26 ቀን 2006 ሰዎቹ እንዲቀርቡ ያዘዘ ሲሆን በቀጠሮው ቀን ይቅረቡ አይቅረቡ የሚታወቅ ነገር የለም ብለዋል – የሟች ባለቤት ወ/ሮ ፋጡማ፡፡
የ58 አመት ጐልማሳ የነበሩት ኢ/ር ጀሚል ሃሰን፤ ኪናንጀሚልና ኢፕቲሀጅ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ከኮሜርስ በአካውንቲንግ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ትምህርት መማራቸውንም ባለቤታቸው ወ/ሮ ፋጡማ ተናግረዋል፡፡ ከረጅም ዓመት በፊት “ርብቃ” የተባለ መጽሐፍ የተረጐሙ ሲሆን መታሰቢያነቱንም ለገዳይ አያት ሻለቃ ሱልጣን እንዳደረጉ ከመጽሐፉ መረዳት ይቻላል፡፡ ስድስት ያልታተሙ የትርጉም ስራዎች እንዳሏቸውና በመጨረሻው የእድሜ ዘመናቸው አካባቢ “the three Cup of Tea” የተሰኘ መጽሐፍ ተርጉመው ለህትመት ሲያዘጋጁ እንደነበር ባለቤታቸው ተናግረዋል፡፡ “አፒክስ” የተሰኘ የጉዞ ወኪል ድርጅት የነበራቸው ኢ/ር ጀሚል፤ “ኦፕቲፋም” የተሰኘ የኔትወርክ ቢዝነሳቸውን በማናጀርነት ይመሩም እንደነበር ታውቋል፡፡
ኢ/ር ጀሚል ከመሞታቸው በፊት “ሁሉንም ሰው ይቅር ብያለሁ፤ ገዳዮቼንም ጭምር” የሚል ቃል መናገራቸውን፣ ተጨማሪ መልዕክት ለማስተላለፍ እስኪርቢቶ ጠይቀው መፃፍ እንደተሳናቸው ባለቤታቸው በእንባ ታጅበው ነግረውናል፡፡ “ይህን ጉዳይ አይቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ፤ ልጆቼም እኔም ፍትህ እንሻለን” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

SOURCE, addis admas